Screenshot 2025-05-19 at 5.24.17 PM

በዘንድሮው የበጋ ወቅት በየሰፈራችን ያሉት የመዋኛ ገንዳዎች ያለገደብ አገልግሎት ይሰጣሉ። በተለይ ልጆች ያላቸው ቤተሰቦች እነዚህን የመዋኛ መዝናኛዎች ያዘወትራሉ። እርስዎም በዚህ በጋ የመዋኘት እቅድ ካለዎት ወይንም ልጆችዎን ይዘው ወደ መዋኛ ቦታዎች የሚሄዱ ከሆነ የመዋኛ ልብስ መረጣ ላይ እንዲያስቡበት ይመከራል። የአኳቲክ ሴፍቲ ከኔክሽን የሰራው ጥናት እንደሚያሳየው ሁሉም የመዋኛ ልብሶች እኩል በአይን አይታዩም ይላል። እንደ ጥናቱ ከሆነ የምንለብሰው የዋና ልብስ ቀለም የመስጠምና የመሞት አደጋን በተወሰነ መልኩ ይቀንሳል ይላል። በጥናቱ እንደታየው [ከስር በምስል እንደተቀመጠው] ደማቅ ቀለም ያላቸው ብርቱካናማ ልብሶች በዋና ገንዳ ውስጥ በደንብ የሚታዩ ሲሆን ፈዛዛ ቀለም ያላቸው ልብሶች ደግሞ ብዙም አይታዩም። በዋና ገንዳዎች ሰማያዊ ወይንም አረንጓዴ ቀለም ልብሶች ለመታየት ከባድ ሲሆኑ በሀይቆችና ወንዞች ደሞ ግራጫና ነጭ ልብሶችን ለማየት አዳጋች ነው።
በመስመጥ አደጋ ጊዜ የዋና ልብስ የመታየት እድሉ ትልቅ የሆነ ልብስ ያደረገን ዋናተኛ ለማትረፍ የተሻለ እድል አለ። ለዚህም ደማቅ ቀይ ወይንም ብርቱካናማ ቀለም ያላቸው ልብሶች በነፍስ አድን ጠላቂ ዋናተኞች ተመራጭ ናቸው ሲል የአላይቭ ሶሉሽንስ ድረገጽ አስታውቋል።


በተጨማሪም ባለሞያዎች የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች እንድታደርጉ ይመክራሉ።

  • ውኃ አቅራቢያ ልጆችዎን ይቆጣጠሩ – ልጄ ዋና ይችላል፤ ወይንም ልጄ ውሃ ውስጥ መግባት እንደሌለበት ያውቃል ብለው በፍጹም እንዳይዘናጉ። አደጋዎች ሳይታሰብ ሊደርሱ ስለሚችሉ ሁሌም ልጅዎ ከአይንዎ እንዳይርቅ አይዘናጉ።
  • የላይፍ ጃኬት ያድርጉ – የነፍስ አድን ጃኬት እንዲያደርጉ በሚመከርባቸው ቦታዎች በሙሉ የላይፍ ጃኬት ያድርጉ።
  • ከተፈቀዱ ቦታዎች ውጪ በፍጹም አይዋኙ – ለዋና የተከለከሉ ቦታዎች ምክንያት አላቸው። ምንም ያህል በራስዎ ቢተማመኑ ለመዋኘት በተከለከሉ ቦታዎች አይዋኙ።
  • ከአልኮል መጠጥይቆጠቡ – ልጆችዎን ወደ ውኃ ዳርቻ/ የመዋኛ ገንዳ የመሳሰሉት ቦታዎች ይዘው ሄደው እንደሆን ራስዎንና ቤተሰብዎን በአግባቡ መቆጣጠር እንዲችሉ ከአልክሆል መጠጥ ራስዎን ያቅቡ።
  • ልጆችዎን መሰረታዊ ዋና ያስተምሩ፡ በአካባቢዎ ባሉ የመዋኛ ገንዳዎች ወይንም ማስተማሪያ ቤቶች በመውሰድ ልጆችዎን ዋና ያስተምሩ። ዋና ልክ እንደ መንጃ ፍቃድና ሌሎች ትምህርቶች በህይወት ለመኖር ወይንም ለመቆየት መሰረታዊ ክህሎት ነው።
  • ሰዎች ሲሰምጡ ምን እንደሚያደርጉ (የመስመጥ ምልክቶች) ምን እንደሆኑ ይወቁ – ብዙውን ጊዜ ሰዎች ሲሰምጡ በፊልም እንደምናየው ጩኸትና መንቦራጨቅ ላያሳዩ ይችላሉ። በአብዛኛው ሰዎች ሲሰምጡ በፍጥነትና ድምጽ ሳያሰሙ ነው።

በተጨማሪም ወደ ውኃ አካላት ከመሄድዎት በፊት ዕቅድ ይኑርዎት። የሚሄዱበት የውሃ አካል የመዋኛ ገንዳ ነው፤ ወንዝ ነው፤ ሀይቅ ነው ወይስ ውቅያኖስ ነው የሚለውን ይለዩ። ከዛም

  • ለሚሄዱበት የውሀ አይነት ተስማሚ የሆኑ ቁሶች ያዘጋጁ። ዋና የማይችል ሰው ከመሀል ካለ በክብደታቸው ልክ የሚሆን የላይፍ ጃኬት ይያዙ። የመጀመሪያ እርዳታ መስጫ ቁስ፤ ሰን ስክሪን፤ ውኃ፤ መክሰስና የመሳሰሉትን ይያዙ።
  • ወደ ውሃ ከመግባትዎ በፊት የአየሩን ሁኔታ፤ የውኃውን ሁኔታ፤ የማዕበሉን አይነት ያጥኑ። በአካባቢው የነፍስ አድን ሰራተኛ መኖሩንም ያረጋግጡ። በተለይም ሞገድ ባለባቸው ውቅያኖሶች ለመዋኘት ከሄዱ ወደ ውሀው ጎትቶ ስለሚወስደው ሪፕ ከረንት በደንብ ይወቁ።
  • ግልጽ ህግ ያስቀምጡ። ልጆችዎት ብቻቸውን ውኃ መግባት እንደማይችሉ ይንገሯቸው። በውሀ ውስጥ እያሉ ከአላስፈላጊ ልፊያም እንዲታቀቡ ያርጓቸው። ከአዋቂዎቹ መሀከል ደሞ ልጆቹን የሚጠብቅ ሰው ይመድቡ።ብዙ ጊዜ ሰዎች ሳይነጋገሩ “አንተ እየጠበቅ መስሎኝ ነበር” በሚል የሰዎች ህይወት ይጠፋል።
  • በየተወሰነው ሰዓት እረፍት አድርጉ። መክሰስ ብሉ ውኃ ጠጡ።

መልካም የበጋ ወራት ይሁንላችሁ።

About Author

ይህን መረጃ ለወዳጅ ዘመዶችዎ ሼር ያርጉት

Sign In

Register

Reset Password

Please enter your username or email address, you will receive a link to create a new password via email.