
ባሳለፍነው ሳምንት ዴይሊ ሜይል አገኘሁት ባለው ረቂቅ የሪያሊቲ ሾው ፕሮፖዛል ላይ ታየ የተባለው ረቂቅ ሀሳብ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ከርሟል።በዚህ ባለ 35 ገጽ ረቂቅ መሰረት የሪያሊቲ ሾዉ መጠሪያ “ዘ አሜሪካን” እንደሆነና 12 ስደተኞች ከኒውዮርኩ ታሪካዊ የስደተኞች ማረፊያ ከኤሊስ ደሴት ተነስተው በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች በባቡርና በመሳሰሉት መጓጓዣዎች በመጓዝ በየስቴቱ ባህልና ወግ ባሉ ውድድሮች የሚካፈሉ ሲሆን ከነዚህም እንደምሳሌ የቀረቡት በሳንፍራንሲስኮ የወርቅ ማዕድን ቁፋሮ፤ በዊስኮንሲን በውኃ ላይ ባለ እንጨት ላይ ባላንሳችውን ጠብቀው መቆየት፤ በኮሎራዶ በአየር በተሞላ ጀልባ በአደገኛ ፏፏቴ መሽቀዳደም፤ በፍሎሪዳ ሮኬት መገንባትና በዲትሮይት ደሞ የፎርድ መኪና ሞዴል ቲን መገንባት ይገኙበታል። የየሳምንቱ የፕሮግራሙ አሸናፊዎች ታዲያ የአሜሪካንን ባህልና ታሪክ የሚያንጸባርቅ ሽልማት የሚያገኙ ሲሆን ከፕሮግራሙ የሚባረሩ ሰዎች የኢሚግሬሽን ኬዝ ላይ ምንም አሉታዊ ተጽዕኖ አይኖረውም ተብሏል።
የዚህ ሾው ሀሳብ አፍላቂ የሆነ በካናዳ የተወለደውና ራሱ የቀድሞ ስደተኛና የአሁን አሜሪካዊ ሮብ ዎርሶፍ ሲሆን ሮብ ከዚህ ቀደም ባቀረባቸው ደክ ዳይናስቲና ዘ ሚሊየነር ማችሜከር ሪያሊቲ ሾዎች ይታወቃል።
የዲፓርትመትን ኦፍ ሆምላንድ ሴኩሪቲ ቃል አቀባይ ትሪሻ ማክሎሊን በበኩላቸው ይህ ሀሳብ በቢሯቸው እየተገመገመ እንደሆነና እስካሁን ግን ፍቃድም ሆነ ክልከላ አልተደረገበትም ሲሉ ተናግረዋል። በሚዲያዎች እንደተነገረውም የዲ ኤች ኤስ የበላይ የሆኑት ክርስቲ ኖኤም ይህንን ረቂቅ እንዳላዩትና ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ እንደሌላቸው ቃል አቀባዩአ ተናግረዋል። በሌላ በኩል ግን ዘ ዴይሊ ሜይል በዘገባው ክርስቲ ኖኤም ሀሳቡን ደግፈውታል ሲል አስታውቋል።
ይህ ሀሳብ በርካታ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎችን አፍርቷል።በአንድ ወገን የሀሳቡ አቅራቢና አንዳንድ ሌሎች ደጋፊዎች ፕሮግራሙ በትክክል የሜሪካንን ባህልና ማንነት ለህዝብ ያስተዋውቃ ብለው ሲከራከሩ በሌላ ወገን ደሞ ይህ ስደተኞችን እንደ ሀንገር ጌምስ ባለ ትርዒት ማሳተፍና በሰዎች ችግር መዝናኛ መስራት የማህበረሰባችንን የሞራል ዝቅጠት ማሳያ እንደሆነ ይናገራሉ።