
ከሰሞኑ በአገረ አሜሪካን ከደቡብ አፍሪካ የመጡ ነጭ ስደተኞች የአሜሪካ ባንዲራ እያውለበለቡ በመግባታቸው በርካታ የቀኝ ዘመም ፖለቲከኞችና ደጋፊዎች ዘንድ ከአሜሪካ ባህልጋ ለመዋድ ያሳዩትን ቀናዒነት በማድነቅና ሌሎች ስደተኞች ደሞ እንዴት የራሳቸውን ባንዲራ ብቻ እያውለበለቡ እንደሚመጡ በመናገር ሲያነጻጽሩ ነበር።
ከዚህ ቀደም በነበሩት የዴሞክራት አገዛዞች ወቅት ብዝሀዊነት እንደ አንድ ትልቅ እሴት ተይዞ ሰዎች ባህሌና ማንነቴ የሚሉትን በነጻነት እንዲያንጽባርቁ ከመፍቀድ አልፎ በሰፊው ድጋፍ ሲደረግበት የቆየ አሰራር ነበር።
አሁን የፌደራል መንግስቱን በሚያስተዳድረው የትራምፕ መንግስት ደግሞ የፖሊሲ አቋሙ መጀመሪያ አሜሪካ የምትቀድም በመሆኑ የሌላን አገር ባህል ማክበርና ማንጸባረቅ ባይከለከልም ቀድሞ እንደነበረው አይነት ድጋፍ ግን የለውም።
በዚህ መንግስት ተዘውትሮ የሚሰማውን ይህን አኃዳዊነትና የመዋሃድ ጽንሰ-ሀሳብ ስደተኞች ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል የሚለውንና በጥቅሉ ምን እንደሆነ እንየው።
መዋኃድ (Assimilation) በቀላሉ በአዲሱ አገር ውስጥ ካለው ሕይወትና ዘይቤ ጋር መላመድን ያመለክታል – ልክ እንደ ቋንቋ መማር፣ የአካባቢውን ልማዶች መረዳት እና የህብረተሰቡ አካል መሆን ማለት ነው። ከአገሩ ባህል፤ ቋንቋን ልማዶችጋ መዋኃድ መቻል በርካታ በሮች እንዲከፈትልዎት ምክንያት ሊሆን ይችላል።
ከነዚህ አንዱና ዋነኛው ቋንቋ ነው። ግን ደሞ በመዋኃድ ስም የራስን ማንነት የማጣት ፍራቻ እንዲሁም የራስዎን ባህል ጠብቆ ማቆየት እና ከአዲስ ባህል ጋር መላመድ መካከል የራስዎን ሚዛን ለማግኘት መቸገርን ሊያመጣ ይችላል።
ከቋንቋ በተጨማሪ መላመድ በአካባቢያዊ ጉዳዮች፤ በምርጫ፤ በበጎ ፍቃድ ተግባራት፤ በስራ፤ በአካባቢያዊ በዓላት ላይ በመሳተፍ፤ በስራ በኩል መዋሀድ ይመጣል። ከላይ እንደተጠቀሰው በዋናነት ቋንቋ አንዱ ሲሆን የ2023 ዓ.ም ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ በቋንቋቸው ጎበዝ የሆኑ ስደተኞች ከሌሎቹ አንጻር ገቢያቸው ከ15 እስከ 20% የተሻለ እንደሆነ ተነግሯል።

በተጨማሪም በየአካባቢው በሚዘጋጁ ፌስቲቫሎች፤ ክብረ በዓላትና የበጎ ፍቃድ ፕሮግራሞች ላይ መሳተፍ ለስደተኞች ከሰዎችጋ መተዋወቂያ ከመሆኑ በተጨማሪ ለልጆቻቸው በትምህርት እንዲበረቱና የያገባኛል፤ ይህ የኔም ቦታነው በሚል መንፈስ እንዲኖሩ እንደሚያግዝና ሲያድጉ አገሪቱን በባለቤትነት መንፈስ እንዲገነቡና ጥሩ ዜጎች እንዲሆኑ እንደሚረዳ ተጠቁሟል።

ሆኖም ለስደተኞች ከአዲሱ ባህልጋ ከመተዋወቅ አልፎ መዋኃድ ቀላል ላይሆን ይችላል። የራስ ማንነት የተገነባበትን ቋንቋ፤ ባህል ወይንም የአኗኗር ዘይቤ ጥሎ አዲስ ማንነትን መላበስ ከባድ ነው። በተጨማሪም አገሩ አውቆም ይሁን ሳያውቀው ስደተኞችን የማግለል አባዜ አለበት። በ2024 የተሰራ መጠይቅ ላይ እንደታየውና በመጠይቁ ከተሳተፉ ስደተኞች 60% ያህሉ መገለል እንደደረሰባቸውና በዚያም ምክንያት መዋኃድ እንደከበዳቸው ተናግረዋል።

እንዴት ነው ሁለቱን ማጣጣም የሚቻለው?
የራስን ማንነት ሳይጥሉ ግን ደሞ ከዚህ አገር ባህልና ልማዶችጋ ለመዋኃድ መሞከር ከባድ ቢመስልም ብዙዎች አድርገውታል፤ ደሞም ተሳክቶላቸዋል። ከስር ያሉትም ከብዙ በጥቂቱ ናቸው።
- ቋንቋውን መማር – በተለይም የፕሬዘደንት ትራምፕ አስተዳደር የእንግሊዝኛን ቋንቋ ብሄራዊ የስራ ቋንቋ እንዲሆን ካደረጉት በኋላ ይህ ለነገ የሚተው ጉዳይ መሆን የለበትም። ይህ ማለት ግን በአንድ ቀን፤ በአንድ ሳምንት፤ በአንድ ወር ወይንም በአንድ አመት ቋንቋውን መቻል አለባችሁ ማለት አይደለም። በራሳችሁ ፍጥነት በመማር ራስን መለወጥ ግን አይነተኛ ተግባር ነው።
- በአካባቢያችሁ ባሉ ጉዳዮችና ፕሮግራሞች ይሳተፉ – ለምሳሌ ኢትዮጲክ እንደምታደርገው በሞንጎምሪ ካውንቲ ታንክስጊቪንግ ፐሬድ ላይ መሳተፍ፤ ከሰሞኑ ደሞ በማደጎ በወሰድነው የሲልቨር ስፕሪንግ አቬኑ ላይ በሚኖረን የጎዳና ጽዳት የበጎፍቃድ ተግባራትና በመሳሰሉ አካባቢያችሁ ላይ ባሉ ግን ከእናንተና ከእናንተ ማህበረሰብ አልፎ ተርፎ ሌላውን ትልቁን ማህበረሰብ በሚጠቅሙ ጉዳዮ ይሳተፉ።

- የራስን ባህልና ማንነት አለመጣል፤ ለልጆችዎም ማስተማር– መዋኃድ ማለት የራስን ማንነት እርግፍ አድርጎ መጣል አይደለም። ይልቅስ ራሳችንንና ማንነታችንን ይዘን ተጨማሪ ጌጥ ለመሆን ወይንም አገልጋይ ለመሆን የምንገባበት መሆን አለበት።
- እርዳታ ከመጠየቅ ወደኋላ አይበሉ – የከበደዎት ነገር ካለ ወይንም መገለል ከደረሰብዎት በርካታ ለስደተኞች የሚያገለግሉ ተቋማት አሉ። እኛንም [ኢትዮጲክን] መጠየቅ ይችላሉ። መልሱን ባናውቀውም እንኳ ወዴት መሄድ እንዳለብዎት መንገዱን እናሳይዎታለን።
መዋኃድ ባለ ሁለት መንገድ ነው። የእርስዎ አስተዋጾ ይህን አገር የተሻለ እንዲሆን ያደርጋል፤ ይህም አገር እርስዎን ወደተሻለ ህይወት ይወስድዎታል። ትንሽ የሚመስልዎት እያንዳንዱ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ የአገር ግንባታው አንድ አካል ነው።