በኤፕሪል 14 2021 የ58 ዓመቱን ሄርናን ሊቫ የተባለ ግለሰብ በሚሰራበት በቤይሊስ ክሮስሮድ በሚገኘው የታርጌት መደብር ውስጥ ከስራ ባልደረባውጋ ይጣላል፡፡ የጥላቸው መንስዔ ደሞ በወቅቱ የ22 ዓመት ወጣት የሆነው ባዘን በርሄ የተባለው የሄርናን የስራ ባልደረባ ምግቤን ሰርቀኸኛል በሚል ነው፡፡ በበነጋታው ታዲያ ገዳይ መዶሻና ቢላዎችን በመግዛት የግድያ ልምምድ ሲያደርግ እንደቆየ ፖሊስ አሳውቋል፡፡
ማስታወቂያ:- በየጊዜው የምናወጣቸውን መረጃዎች ለማግኘት በፌስቡክና … በቴሌግራም ይከታተሉ:: ለወዳጅ ጏደኞችም ይንገሯቸው::
ይህን ተከትሎም ታዲያ ወጣት ባዘን በኤፕሪል 17 ንጋት 3፡30 ላይ 5100 block of Leesburg Pike አቅራቢያ ባለ የመኪና ማቆሚያ ውስጥ ባልደረባውን በቢላዋ በመውጋትና በመዶሻ በመቀጥቀጥ ለህልፈት ዳርጎታል ሲል ፖሊስ በወቅቱ አሳውቋል፡፡ ባዘን በወቅቱ ወዲያው እጁን ለፖሊስ የሰጠ ሲሆን በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ክስ ተመስርቶበት ፍርዱን እየተጠባበቀ ነበር፡፡
የአሌክሳንድሪያ ነዋሪ የነበረው ባዘን በርሄ ታዲያ ትላንት ጃንዋሪ 30፣ ለመጨረሻ ውሳኔ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን ዳኛው ለ100 ዓመት ወህኒ እንዲወርድ ፈርደውበታል፡፡ በኦክቶበር በነበረው የፍርድ ቤት ቀጠሮ ወንጀሉን እንደፈጸመ ያመነ ሲሆን ለወንጀሉ ያነሳሳውም በውስጡ የነበረው ንዴት እንደሆነ አሳውቋል፡፡ ባልተለመደ መልኩም ባዘን በርሄ ፍርዱን ለመስጠት የተሰየሙትን ዳኛ ሮበርት ስሚዝን ከባድ ቅጣት እንዲጥሉበት የጠየቀ ሲሆን ይህ ከሆነም ማንንም ሰው እንደማይገድል ወይንም ማንም ሰው ላይ ጉዳት እንደማያደርስ ቃል ገብቷል፡፡
ባዘን በርሄ —-ምንጭ፡ የፌርፋክስ ካውንቲ ፖሊስ
ባዘን በርሄ ለዚህ ወንጀል ያነሳሳው ንዴት በዋናነት ከኢሚግሬሽንጋ ያለው ችግር እንደሆነና በተለይም ህጋዊ ሆኖ በአሜሪካ መኖር እንደማይችል ከተነገረው በኋላ በመበሳጨቱ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
የባዘን ጠበቃ የሆኑት ብራንደን ስሎዌን ዳኛው ፍርዱን እንዲያቀሉለት ቢጠይቁም ባዘን ግን ከባድ ፍርድ እንዲሰጠው በመጠየቁ ጥያቄያቸው ውድቅ ሆኗል፡፡
ማስታወቂያ:- በየጊዜው የምናወጣቸውን መረጃዎች ለማግኘት በፌስቡክና … በቴሌግራም ይከታተሉ:: ለወዳጅ ጏደኞችም ይንገሯቸው::
ባዘን በርሄ ትላንት በነበረው የፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ ለፍርድ ቤቱ የመጨረሻውና በጣም ከባዱ ቅጣት ካልተሰጠው ተጨማሪ ሰው እንደሚገድል ለፍርድ ቤቱ የተናገረ ሲሆን ይህን ተከትሎ ዳኛው የ100 ዓመት እስራት ፈርደውበታል፡፡ ባዘን አክሎም “ሟችን የገደልኩበት ሁኔታ አሰቃቂ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ የሟች ቤተሰቦች እንዲያውቁት የምፈልገው በተቻለኝ መጠን ከ1 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ህይወቱና ለማጥፋት ሞክሬያለሁ” ብሏል ሲል ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
ለጥቆማው ራስ አስራትን እናመሰግናለን፡፡