የዲሲ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ ተጠብቆ እንዲቆይ ለማደርግ ያሰበ ፕሮግራም በዲሲ የህዝብ ቤተ መጻህፍት ተዘጋጀ። ይህ ፕሮጀክት ከላይብረሪ ኦፍ ኮንግረስ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ አማካይነት ተግባራዊ እንደሚሆንም ተነግሯል። በአመቱ መጀመሪያ ላይብረሪ ኦፍ ኮንግረስ ያዘጋጀውን የ2024 ኮኔክቲንግ ኮሚውኒቲስ ዲጂታል ኢኒሼቲቭ ውድድር ከተወዳደሩ መኃል ስድስት ተቋማት ያሸነፉ ሲሆን የዲሲ የህዝብ ቤተ-መጽኃፍት ከነዚህ አንዱ ነው።
ከዚህ ፕሮጀክት በተገኘ ፈንድ አማካኝነትም የዲሲ የህዝብ ቤተ መጽሀፍት የዲሲ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ ለመሰነድ እንዳቀደና ማንኛውም ሰው በዚህ ፕሮጀክት ላይ መሳተፍ እንደሚችል ተነግሯል። ይህ ፕሮጀክትም የዲሲ የህዝብ ቤተመጽኃፍት ከአርቲስት ጸደይ መኮንንና ጋዜጠኛ ሀና ጊዮርጊስ ዮኃንስጋ በመተባበር የሚሰራ ፕሮጀክት እንደሆነ በጁን 18 2024 የወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
በዚህ ፕሮግራም ላይ በዲሲ የኢትዮጵያውያንን ፎቶግራፎችና፤ የአፍ ታሪኮች ይሰነዳሉ። በተጨማሪም ባህላዊ ፕሮግራሞችና የስነጥበብ ውጤቶች ይዘጋጁበታል።
እነዚህ ስራዎችም የዲሲ ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ ባለፈው መቶ አመት በከተማዋ ላይ ያሳረፈው ተጽዕኖን የሚያጎሉ ሲሆኑ ማህበረሰቡም በነዚህ ፕሮግራሞች ተገኝተው ያበረከቱትን አስተዋጾ እንዲመለከቱ ዕድል እንደሚኖራቸው ተነግሯል።
ይህ ፕሮጀክት ታዲያ ቅዳሜ ኖቨምበር 16 2024 ከሰዓት 1pm እስከ 4pm ድረስ ዲሲ 2714 Georgia Ave NW, Washington, DC 20001 ላይ በሚገኘው በሳንኮፋ መጻህፍት ፤ ቪዲዮና ቡና ቤት ፕሮግራም አዘጋጅቶ ማንኛውም ሰው እንዲታደመው ጋብዟል። በዚህ ፕሮግራም ላይ ፎቶዎቻችሁን በዲሲ ላይብረሪ የማስታወሻ ማህደር እንዲካተት ማረግ የሚቻልበትን እድልም አዘጋጅተዋል። በተጨማሪም በፕሮግራሙ ላይ ቀደምት የዲሲ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ ማዳመጥ የሚቻልበት መድረክና በራስ ባንድ የተዘጋጀ የጃዝ ሙዚቃ ተዘጋጅቷል።
መረጃውን ያገኘነው ከዲሲ የህዝብ ቤተ-መጽኃፍት ድረገጽ ነው።