በአሜሪካዊው የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ በዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ ስም የተሰየመውና የማርቲን ሉተር ኪንግን ራዕይ ለማሳካት የሚሰራው ዘ ኪንግ ሴንተር የተባለው ተቋም በመጪው ዓመት ጃንዋሪ 11 2025 በአትላንታ ጆርጂያ በስራቸው ለሌሎች ህይወት ደህንነት የሚሰሩና በምግባራቸው አርአያ የሆኑና የሁሉንም የሰው ልጆች ህይወትን ለማሻሻል እየሰሩ የሚገኙ ግለሰቦችንና ተቋማትን ለመሸለም Beloved Community Awards የተሰኘ ፕሮግራም አዘጋጅቷል።
በዚህ የዕውቅና ፕሮግራም ላይ ታዲያ ይህንን ታሪካዊ ሽልማት ከሚያገኙ ሰዎች መኃከል አንዱ ሄማን በቀለ እንደሆነ ተቋሙ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።
የዘንድሮ አመት መሪ ቃላቸውም ‘Mission Possible: Protecting Freedom, Justice, and Democracy in the Spirit of Nonviolence365.’ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል። ይህ የሽልማት ስነ-ስርዓት አትላንታ ሴንቲኒያል ፓርክ በሚገኘው ኦምኒ አትላንታ ሆቴል ጃንዋሪ 11 2025 6pm የሚከናወን ይሆናል::
ሂማን በቀለ በ2023 የቆዳ ካንሰርን ሊፈውስ የሚችል የገላ ሳሙና ላይ ባደረገው ምርምር የአመቱ ታዳጊ ሳይንቲስት በመባል ተሸልሞ የነበረ ሲሆን ይህን ተከትሉም በርካታ ሽልማቶችን ተቀዳጅቷል። ታዳጊ ሂማን በቀለ የአመቱ ምርጥ ታዳጊ በመባል በታይም መጽሄት እውቅና እንዳገኘ ይታወሳል።