የ33 አመይ ወጣት የሆነው ቶሪ ሙር ባሳለፍነው አርብ በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ በ2022 የ8 ወር እርጉዝ የነበረችውን የ26 አመት ወጣት እጮኛውን ዴኒስ ሚድልተንንና ያልተወለደ ልጃቸውን በመግደል ወንጀል ወንጀለኛ ተብሎ ተፈረደበት።
ቶሪ ሙር በሞንጎምሪ ካውንቲ ታሪክ የመጀመሪያው ያልተወለደ ጽንስን ነፍስ በማጥፋት ወንጀለኛ የተባለ ሰው ሆኗል።
ወንጀሉ በተፈጸመበት ወቅት የሙር እጮኛ የሆነችው ዴኒስ ሚድልተን የ8ወር ተኩል ነፍሰጡር የነበረች ሲሆን ፖሊሶች ተጠርጣአሪውን በሌላ ወንጀል ጠርጥረውት ለፍተሻ ቤቱ ሲሄዱ በመበስበስ ላይ የሚገኝ ሬሳ እንዳገኙ ከዚህ ቀደም በሰራነው ዘገባ አስነብበን ነበር።
ቶሪ ሙር ለዚህ ወንጀል ፍርዱን ለመቀበል ለማርች 28 2025 ቀጠሮ የተሰጠው ሲሆን ከዚህ ወንጀል በተጨማሪም በ2022 የጋዝ ስቴሽን ሰራተኛ የነበሩትን የ61 አመቱን አቶ አያሌው ወንድሙን ነፍስ በማጥፋት ወንጀል ፍርዱን እየተጠባበቀ ይገኛል ሲል የካውንቲው አቃቤህግ አስታውቋል።
ግድያው የተፈፀመው ዲሴምበር 8 2022 በኒው ሃምፕሻየር ጎዳና 11100 ብሎክ ውስጥ ባለው የሼል ጋዝ ማደያ (Dash In Convenience Store) ነው። ፖሊስ በእለቱ ከከሰዓት 3፡30 ላይ የስልክ ጥሪ ደርሶት በቦታው ሲደርስ በጋዝ ማደያው ሱቅ ውስጥ ሰው በጥይት ተመቶ ያገኙ ሲሆን ይህ ሰውም በኋላ ላይ በተደረገ ማጣሪያ በማደያው ተቀጥረው የሚሰሩት የ61 አመት አመት አዛውንት የሆኑት አቶ አያሌው ወንደሙ እንደሆኑ አሳውቋል፡፡ በፖሊስ ምርመራ መሰረት በሙርና በአቶ አያሌው መኃል መነሻው ምን እንደሆነ ያልታወቀ እሰጥ አገባ እንደነበራቸውና በኋላም ይህ እሰጥ አገባ ወደ አካላዊ ግጭት (ድብድብ) ተቀይሮ ተጠርጣሪው ሽጉጥ አውጥቶ በሟች ላይ በርካታ ጊዜ እንደተኮሰባቸውና ለሞት እንደዳረጋቸው ፖሊስ አሳውቋል።
በወቅቱ ፖሊስ ተጠርጣሪን ተከታትለው ይኖርበታል ወደተባለው ኢንክሌቭ አፓርታማ የመበርበሪያ ወረቀት ይዘው በመሄድ በቤቱ ባደረጉት ፍተሻ ሌላ መበስበስ የጀመረና ማንነቱ ያልታወቀ ሰው ሬሳ እንዳገኙ አክለው ተናግረዋል። ይህ ሬሳም በኋላ ላይ የእጮኛው ዴኒስ እንደነበር ታውቋል።
ለጥቆማው ጆቫኒ ዮሐንስን እናመሰግናለን።