12/11/2024
ስዕል 1፡ ከቤታቸው የሚፈናቀሉ ተከራዮች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል (ሊን ዶ/ፍሊከር)

ስዕል 1፡ ከቤታቸው የሚፈናቀሉ ተከራዮች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል (ሊን ዶ/ፍሊከር) https://www.flickr.com/photos/lmdo/5803417318/in/photolist-9QQ2Mh-bn7WxV-6KMRWV-6KMRJ4-6KMNyH-5AhEBN-6KRU4h-Z4yekf-okbzQV-6KRUbC-6KRUju-6KMR6v-6KRXro-6KMKMz-6KMLVH-6KMRvB-9hBZMB-aDDUAk-6KRS21-6KRUX3-6KMMTr-6KRUu3-Hk2AFx-6KMLqT-6KMNeB-6KMKE4-qPs62R-6KMPY4-aEVgfk-6KMKtv-6KMPkR-6KRWxA-6KMJCR-okbGYm-6KRXN3-atpRLi-2dKn3sE-okc44R-6KMNqc-6KMMJg-6KMQmK-6KMP1K-okc4EF-6KMRiT-2dQBAqh-6KMSc8-6KMQap-atqrHk-6KMLL6-6KMJSB

ያለዎትን ጊዜ፤ ሌሎች አማራጮችና የህግ አገልግሎት መፍትሄዎችን ካወቁና በቂ መረጃ ካለዎት ከቤትዎ ከመባረር የተሻለ ውጤት ያገኛሉ፡፡

በአቢጌል ሂጊንስ ለ 51st.news የተጠናቀረ

በኢትዮጲክ የተተረጎመ

በዋሽንግተን ዲሲ ከኪራይ ቤታቸው የሚፈናቀሉ ነዋሪዎች ቁጥር እለት ተለት እያሻቀበ ይገኛል፡፡ ይህ መጣጥፍ በተጻፈበት ወቅት በፍርድ ቤት ከመኖሪያ ቤታቸው እንዲወጡ ወይንም እንዲፈናቀሉ የተወሰነባቸው ተከራዮች ቁጥር 1493 ነው፡፡ ይህም ከኮቪድ ፓንደሚክ በኋላ ሬከርዱን የያዘ ትልቅ ቁጥር ሲሆን፤ ከኮቪድ 19 በፊት የቤት ኪራይ ድጋፍ ብዙም ባልነበረበት ወቅት ከነበረው ቁጥርጋ ተቀራራቢ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

የዲሲ ካውንስል በቅርቡ ያሳለፈው አዲስ ህግ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ተከራዮች የድንገተኛ የቤት ኪራይ ድጋፍ ስር የነበራቸውን ያለመፈናቀል ጥበቃ እንደሚሸረሽርና ለመፈናቀል ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው የመኖሪያ ቤት ፍትህ ታጋዮችና የህግ ባለሞያዎች ስጋት ገብቷቸዋል፡፡

በዋሽንግተን ዲሲ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች በቂ የሚባል የመኖሪያ ቤት አቅርቦት የለም፡፡ እንደምሳሌም ለ100 በድህነት ለሚኖሩ የዲሲ ነዋሪዎች 33 የዝቅተኛ ገቢ መኖሪያ ቤቶች ብቻ ነው ያለው፡፡ በከተማው የፌደራል ቤቶች እገዛ ቫውቸር ተጠባባቂ ምዝገባ ላለፉት በርካታ አመታት ዝግ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የዲሲ ተከራዮች ታዲያ በየጊዜው እያሻቀበ ያለውን የቤት ኪራይ ለመክፈል ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡ በከተማው ካሉ ተከራዮች ታዲያ ከ14% በላይ የሚሆኑት ያልተከፈለ የቤት ኪራይ እዳ አለባቸው፤ ይህም እዳ በዋናነት ከቤታቸው ለመፈናቀል ምክንያት ሆኗል፡፡

በኔይበርሁድ ሌጋል ሰርቪስ ፕሮግራም በተባለው ለትርፍ ያልተቋቋመ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት አዳም ማርሻል ስለጉዳዩ ሲናገሩ “በህይወት ከባድ ጠባሳን ተተው ከሚያልፉ ጉዳዮች አንዱ ተከራዮችን ከሚኖሩበት ቤት በጉልበት ማፈናቀል ነው”” ብለዋል፡፡ አክለውም “በወንጀል ጉዳዮች ላይ ከሚኖሩ ነጻነትን የማጣት ቀጥሎ በሰዎች ልጆች ላይ ሊኖር የሚችል ሁለተኛው አስከፊው የፍርድ ቤቶች ውሳኔ ይህ እንደሆነ ይሰማኛል” ብለዋል፡፡

በዋሽንግተን ዲሲ ከ2023 ወዲህ የቤት አልባዎች (የጎዳና ተዳዳሪዎች) ቁጥር በ14% ጨምሯል፡፡ ተከራዮችን ከቤት ማፈናቀል ደሞ ለዚህ አስተዋጾ እንደሚኖረው ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ሲፈናቀሉ ወደጎዳና ከመውጣት አንስቶ፤ ስራ ማጣትና ድብርት/ድባቴን ሊያስከትልባቸው ይችላል፡፡ ከዛም አልፎ ለወደፊት ሌላ የሚከራይ ቤት እንዳያገኙ ይህ የፍርድ ቤት ዶሴ እንቅፋት ይሆንባቸዋል፡፡

በተጨማሪም ቁጥሮች እንደሚያሳዩት ሰዎችን ከመኖሪያ ቤታቸው ማፈናቀል ለሁሉም የከተማው ነዋሪ በእኩል አይተገበርም፡፡ ለምሳሌ በዲሲ ዋርድ 8 በጉልበት ከቤታቸው እንዲወጡ የሚደረጉ ተከራዮች በዋርድ 2 ከሚገኙት ተከራዮች በ13 እጥፍ የሚጨምር ሲሆን በጠቅላላው 60 ከመቶ የሚሆኑት መፈናቀሎች የሚደረጉት ከአናኮስትያ ወንዝ በስተምስራቅ በሚገኘው ሳውዝ ኢስት ዲሲ ነው፡፡ ይህም መልክዐ፟ምድራዊ ክፍፍል የሚያሳየው በዋሽንግተን ዲሲ ጥቁሮች ከነጮች በበለጠ ከመኖሪያ ቤታቸው እንደሚፈናቀሉ ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃም ጥቁሮች ከነጮች በእጥፍ ከቤታቸው እንዲለቁ በፍርድ ቤት ክስ እንደቀረበባቸው ታይቷል፡፡


ማስታወቂያ

ይህ ሁሉ ሆኖ ታዲያ በዋሽንግተን ዲሲ ከሌሎች እጅግ የተሻለ የተከራዮች መብትን የሚያስከብሩና ማፈናቀልን የሚከላከሉ ጥበቃዎች አሉ፡፡ ተከራዮች እነዚህን የመብት ጥበቃዎች ካወቁ ራሳቸውን ከቤት አልባነት ሊከላከሉና የተሻለ መፍትሄ ሊያገኙ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡ እዚህ ላይ ማሳሰብ የምንፈልገው ይህ መጣጥፍ በህግ ባለሞያዎች አልተጻፈም፡፡ የህግ ምክርም እይደለም፡፡ ሆኖም መረጃውን ለማጠናቀር በርካታ የህግ ባለሞያዎችን፤ የተከራይ መብት ተሟጋቾችን፤ የተከራይ ማህበራትን እንዲሁም የመኖሪያ ቤት ፍትህ ተሟጋቾችን በማነጋገር ተከራዮች ከቤታቸው እንዲወጡ ወረቀት ሲደርሳቸው (eviction notice) ምን ምድረግ እንዳለባቸው የመፍትሄ ሀሳቦችን አጠናቅረናል፡፡ እነሆ

  1. የደረሰዎትን ቤቱን ለቀው ይውጡደብዳቤ (eviction notice) ችላ አይበሉ፡፡ በቀጠሮዎት ወቅት ፍርድ ቤት ይሂዱ

ብዙውን ጊዜ የፍርድ ቤት መጥሪያ የደረሳቸው ተከራዮች በፍርድ ቤት ቀጠሯቸው ቀን በፍርድ ቤት አይገኙም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ በርካታ ቢሆንም ዋነኞቹ ከስራቦታ ፍቃድ አለማግኘት፤ ልጆቻቸውን የሚይዝላቸው ሞግዚት አለማግኘት፤ ወይንም ደሞ ከፍርሀትና ተስፋ ከመቁረጥ የተነሳ እንደሆነ የውድነር ቴናንትስ ዩኒየን ሰብሳቢ ሲየራ ራሚሬዝ ተናግረዋል፡፡ ይህን ተከትሎም በርካታ የዚህ አይነት ክሶች የግራ ቀኙ ሳይሰማ ተከራዮች በቀጠሮ ቀንና ሰዓት ባለመገኘታቸው ምክንያት ብቻ ለአከራዮች ይፈረድላቸዋል፡፡

በዚህ ዘመን ተሟጋቾች በፍርድ ቤት የግድ በአካል መገኘት አይጠበቅባቸውም፡፡ ፍርድ ቤቱ የቀጠሮ ደብዳቤ ለተከሳሾች ሲልክ በአካል ተገኝተው አልያም በቨርቿል ቀርበው መሳተፍ የሚችሉበትን አማራጭ አብሮ ይልካል፡፡ ተከራዮችም በመረጡት መንገድ ጉዳያቸውን መከታተል ይችላሉ፡፡ በነዚህ ቀጠሮዎች በአካልም ይሁን በቨርቿል በመገኘት ብቻ የመፈናቀል ሂደቱን ማዘግየት ይቻላል፡፡

ሲየራ ራሚሬዝ ስለዚህ ሲናገሩም “በዋሽንግተን ዲሲ ተከራዮች ሁሉንም የፍርድ ቤት ቀጠሮዎቻቸውን ሳያዛንፉ ከተከታተሉ የፍርድ ሂደቱን ያዘገየዋል፡፡ ትላንት የፍርድ ቤት ወረቀት ስላገኙ ዛሬ ከቤትዎት ይፈናቀላሉ ማለት አይደለም፡፡ ይልቅስ በተያዘልዎት ቀጠሮ ካልተገኙ ግን በተቃራኒው እርስዎን ከቤትዎ የማፈናቀሉን ሂደት እንዲፋጠን እድል መስጠት ይሆናል፡፡” ብለዋል፡፡

ጠበቃ ለማግኘት፤ ጉዳይዎትንና መከራከሪያዎትን ለማጠናከር ወይንም በጉዳዩ እርግጠኛ ካልሆኑ በቀጠሮት ቀን በፍርድ ቤት በመገኘት የህግ ባለሞያ ምክር ለማግኘት ቀጠሮው እንዲራዘምልዎት እንዲህ በማለት መጠየቅ ይችላሉ (“I request a continuance with all rights reserved to seek legal counsel.” )፡፡

በዲሲ ለነዋሪዎች በተለያዩ ጉዳዮቻቸው ነጻ የህግ ምክር አገልግሎት የሚሰጠው የዲሲ ባር ፕሮ ቦኖ የፍርድ ጉዳይ ላለባቸው ተከራዮች ጠቃሚ መርጃ አዘጋጅቷል፡፡ ከነዚህ መረጃዎች አንዱና ዋነኛው በመጀመሪያ ቀን የፍርድ ቤት ቀጠሮ ቢያንስ 10 ደቂቃ ቀድመው እንዲደርሱ ይመክራል፡፡ ድንገተኛ ጉዳይ ካጋጠመዎትና መገኘት ካልቻሉ ደሞ ለፍርድ ቤቱ በስልክ ቁጥር (202)-879-4879 በመደወል ጉዳዮትን አስረድተው ቀጠሮው እንዲራዘምልዎ መጠየቅ ይችላሉ፡፡ እንደዲሲ ባር ፕሮቦኖ መረጃ ከሆነም ያልተከፈለ የቤት ኪራይ እንዳለብዎት አስቀድመው ከማመን እንዲቆጠቡም አለበለዚያ ግን የእርስዎን ምክንያት  ለማስረዳት እድል እንዳይኖርዎት ያደርጋል አክሎ ይመክራል፡፡

  • ጠበቃ ይያዙ ወይንም የህግ ምክር ከባለሞያ ይጠይቁ

በዲሲ አከራዮችና ተከራዮች ተካሰው ፍርድ ቤት በቀረቡባቸው ጊዜያት አከራዮች 95% ያህል ጊዜ ጠበቃ ሲኖራቸው ተከራዮች ግን 12% ያህል ብቻ ነው በጠበቃ የተወከሉት፡፡ ተከራዮች ጉዳያቸውን የሚከታተልላቸው የህግ ባለሞያ ጠበቃ ካላቸው በቤታቸው የመቆየት እድላቸው በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል፡፡

የአከራይ ተከራይ የህግ ድጋፍ ኔትወርክ (Landlord Tenant Legal Assistance Network) በዲሲ ውስጥ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ተከራዮችን ከመፈናቀል ለመታደግ ያለመና ለተገልጋዮቹ ነጻ የህግ ምክርና ውክልና የሚሰጥ በ6 ተቋማት ቅንጅት የታገዘ ፕሮግራም ሲሆን የህግ ድጋፍ የሚፈልግ ማንኛውም ተከራይ በስልክ ቁጥር (202)-780-2575 በመደወል ወይንም ኦንላይን ይህን ፎርም በመሙላት ተመዝግቦ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላል፡፡ ይህ ተቋም ታዲያ በአመት እስከ 2000 የስልክ ጥሪዎችን እንደሚያስተናግዱና ምንም እንኳ ለሁሉም የህግ ውክልና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ባይችሉ ቢያንስ ግን እንደ ጉዳዩ ለሁሉም ደንበኛ እንደጉዳያቸው የህግ ምክር በመስጠት የተሻለ ውጤት እንዲያገኙ ይረዳሉ፡፡

የገቢ መጠናቸው ከፍ በማለቱ ከየአከራይ ተከራይ የህግ ድጋፍ ኔትወርክ (Landlord Tenant Legal Assistance Network) ድጋፍ ማግኘት ያልቻሉ የዲሲ ነዋሪዎች እንደ ተለዋጭ በዲሲ ባር ፕሮቦኖ የሚተዳደረው የአከራይ ተከራይ መረጃ ማዕከል በአካል በመሄድ ድጋፍ መጠየቅ ይችላሉ፡፡ ይህ ማዕከል በ 510 4th St NW, ሁለተኛ ፎቅ የተከራይ አከራይ ፍርድ ቤት ውስጥ ሩም 223 ውስጥ ይገኛል፡፡ ዘወትር ማክሰኞ ከጧት 10 a.m – 3:00 p.m. ለማንኛውም የዲሲ ነዋሪ አገልግሎቱን ይሰጣል፡፡

የህግ ባለሞያዎች በዋናነት አከራዮች ተገቢውን ህጋዊ መንገድ በመከተል የቤቴን ልቀቁ ማስጠንቀቂያ እንደላኩና እንዳልላኩ በግልጽ ሊያብራሩልዎት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ አከራይዎት እርስዎን ለማስወጣት የግዴታ የፍርድ ቤት የማስወጫ ትዕዛዝ ሊኖረው ይገባል፡፡ በቃል ወይንም በራሳቸው ደብዳቤ መኖሪያ ቤትዎን ለቀው እንዲወጡ ሊያደርጉዎት አይቻላቸውም፡፡ በፍርድ ቤት ቢወሰንም እንኳን በድንገት እንዲወጡ አይደረጉም፤ ይልቅስ በቂ ጊዜ እንዲሰጥዎት ህጉ ያስገድዳል፡፡ የህግ ባለሞያ ታዲያ ይህንን የጊዜ ሰሌዳ በደንብ እንዲረዱትና ምን አይነት የመከላከያ አማራጮች እንዳለዎት ሊያስረዳዎት ይችላል፡፡

ተከራዮች ስለጉዳያቸው መረጃ ወይንም ምን አይነት መንገድ መከተል እንዳለባቸው የሚጠቁም መንገድን ከህንጻው አስተዳደር ብቻ ማግኘት እንደሌለባቸውና የህንጻው አስተዳደር ለተከራዮች ፍላጎት ቅድሚያ ለመስጠት ሊቸገር እንደሚችል የውድነር ተከራዮች ማህበር አስተባባሪ ራሚሬዝ ጠቁመዋል፡፡

  • አይጥ፤ በረሮ ወይንም የሚያንጠባጥብ ቧንቧ አስቸግሮታል? ምናልባትም የቤት አከራዮት ይክፈሉኝ የሚለውን ያህል ገንዘብ እንዲከፍሉ አይጠበቅብዎት ይሆናል፡፡

የዲሲ ተከራዮች በርካታ ከደረጃ በታች በሆኑ የመኖሪያ ቤት ችግሮች ያጋጥሟቸዋል፡፡ ለምሳሌ በቆሻሻ ፍሳሽ የተበከለ ወለል፤ እንደ አይጥ፤ የለሊት ወፍና የመሳሰሉ እንስሳት፤ ጣሪያዎት ወይንም ግድግዳዎት ላይ ሞልድ (ሻጋታ)፤ ወይንም በደንብ የማይሰራ ሙቅ ውኃ ከብዙ በጥቂቱ ነው፡፡ ሆኖም እነዚህ ሁሉ ችግሮች ካሉብዎትና የቤት ኪራይዎን ባለመክፈልዎ ከቤትዎ እንዲወጡ ከተጠየቁ፤ ምናልባትም የቤት አከራይዎት ከጠየቀው እዳ በታች የሆነ እዳ ሊኖርብዎት ይችላል፡፡ አንዳንዴ እንደውም አከራይዎት ራሱ ባለ ዕዳ ሊሆን ይችላል፡፡

በህጉ መሰረት የዲሲ አከራዮች የዲሲ ቤቶች ህግን የሚያሟሉ ቤቶችን ብቻ ለተከራዮች ማቅረብ አለባቸው፡፡ አከራይ ይህንን ህግ ተላልፎ ከሆነና ተከራይ ይህንን መተላለፍ ማስረዳትና ማስረጃ ማቅረብ ከቻለ ፍርድ ቤቱ የተከራዩን እዳ ሊቀንስለት ወይም ጨርሶ ሊምረው ይችላል፡፡ የኔይበርሁድ ሌጋል ሰርቪስ ፕሮግራም ባልደረባ አዳም ማርሻል የዲሲ ቤቶች ህግ ውስብስብ ቢሆንም እንኳ የመኖሪያ ቤቶች ላይ የሚስተዋሉ ግድፈቶች በአብዛኛው ለመረዳት ቀላል እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡

ባለሞያው አክለውም “ግድግዳ እንደ ግድግዳ መስራት አለበት፤ መስኮትም እንደ መስኮት፤ ፍሪጅም እንደ ፍሪጅ፡፡ ግድግዳ እንደ ግድግዳ ካላገለገለ፤ መስኮት በአግባቡ የመስኮት ሚናውን ካልተወጣ፤ ምናልባትም የቤቶችን ህግ ጥሷል ማለት ነው፡፡” ብለዋል፡፡

የውድነር ተከራዮች አስተባባሪ ራሚሬዝ በበኩላቸው በርካታ ተከራዮች በፍርድ ቤት ጉዳያቸው ሲሰማ አንዴ ችግር ውስጥ ገብቻለሁ ብለው ስለሚያስቡ ተጨማሪ ችግር እንዳይመጣ በመፍራት የጥገናና ተያያዥ ጉዳዮችን ማንሳት አይደፍሩም፡፡  ይህ ደሞ ወሳኝ የሆነ መብታቸውን አሳልፈው እንደመስጠት ይቆጠራል፡፡

በሌጋል ኤይድ ዲሲ ሃውሲንግ ዩኒት ውስጥ በተቆጣጣሪ ጠበቃነት እያገለገሉ የሚገኙት አሽሊ ሹልዝ እንደሚሉት “እንደ ቤት ኪራይ ወይም መብራት ወይም ስልክ ያለ አገልግሎትን ለማግኘት ከተስማማን በኋላ ምንም አይነት አገልግሎት ብናገኝ የአገልግሎት ክፍያን የግዴታ መክፈል እንዳለብን ተነግሮናል፡፡ ይህንን ተከትሎም ተከራዮች አብዛኛውን ጊዜ ኪራያቸውን እንዳልከፈሉ ለፍርድ ቤቱ ያምናሉ ፍርድ ቤቱም ይህን ንግግራቸውን ተከትሎ ይፈርድባቸዋል፡፡ ምንም እንኳ የቤቱ ሁኔታ መጥፎ ቢሆንም አስቀድመው በማመናቸው ብቻ ከቤት እንዲፈናቀሉም ሊደረጉ ይችላሉ፡፡”

 የኔይበርሁድ ሌጋል ሰርቪስ ፕሮግራም ባልደረባ አዳም ማርሻል ተከራዮች ስለተከራዩበት ቤት ያሉባቸውን ችግሮች በሙሉ እንዲመዘግቡ ይመክራሉ፡፡ ከቤት አከራይዎትጋ የተለዋወጧቸውን ኢሚይሎችና የቴክስት ሜሴጆች በሙሉ በዝርዝር መያዝ፤ የተበላሹትንና ጥገና የሚያስፈልጋቸውን ችግሮች በፎቶና በቪድዮ ማስቀረት እንዲሁም የቤት ኪራይ የከፈሉባቸውን ደረሰኞች በአግባቡ ማስቀመጥ ወሳኝ እንደሆነ ይመክራሉ፡፡ የዲሲ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለተከራዮች ባዘጋጁት የመረጃ ቋት ተከራዮች ምን አይነት መረጃዎችን ማዘጋጀት እንዳለባቸው ተብራርቶ ተቀምጧል፡፡ በተጨማሪም ሌጋል ኤይድ ዲሲ የተባለው ተቋምም በጥልቅ የተብራራና ተከራዮች የቤት ኪራይ ባለመክፈል የሚያጋጥማቸውን ከቤት መፈናቀል ሲያጋጥም እንዴት እንደሚወጡት ወይም ማድረግ እንዳለባቸው መመሪያ አዘጋጅቷል፡፡

  • በበቀል ወይም በማግለል ተከራይን ማፈናቀል አይፈቀድም

በዋሽንግተን ዲሲ ያሉ ተከራዮች በግላቸው ለሚያደርጓቸው አንዳንድ ጉዳዮች ከቤታቸው ማባረርን ህጉ ይከለክላል፡፡ ከነዚህ ጉዳዮች አንዱ በተከራዮች ማህበር መሰባሰብን፤ የቤት አከራዮች ህግ ሲተላለፉ ለሚመለከተው አካል መጠቆም፤ ወይም ቤቱ እንዲጠገን ጥያቄ ማቅረብን ተንተርሶ አከራይ ተከራይ ላይ እርምጃ መውሰድ አይችልም፡፡ አከራይ ከቤቴ ውጣልኝ የሚል ክስ የመሰረተው በተለይም ተከራዩ ከላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች መሳተፍ ከጀመረ ከ6ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከሆነ ተከራይ ክሱ በበቀል ነው ብሎ መከራከር ይችላል፡፡ አከራይም ክሱ ተከራዩን ለመበቀል እንዳልሆነ ለፍርድ ቤቱ ማሳመን ይኖርበታል፡፡

በተመሳሳይ ከቤት እንዲወጡ የተጠየቁት የህግ ከለላ በተደረገላቸው መደቦችና በተለይም በእድሜ፤ ዘር፤ የአካል ጉዳት፤ የጾታ ዝንባሌ፤ ጾታ፤ ወይንም ልጆች ስላሉዎት ከሆነና ይህንን ማስረዳት ከቻሉ ጉዳዮትን መከላከል ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም ከቤት ውስጥ ጥቃት ወይንም ከጾታዊ ጥቃትጋ ከቤት ማፈናቀል ተያያዥ መሆን አይችልም፡፡

  • ከተከራይ መብት ማህበራትጋ ይገናኙ

የውድነር ተከራዮች ማህበር በየሳምንቱ ቅዳሜ ጧት እየተገናኘ በህንጻው ላይ ያሉ ተከራዮችን በተለይም ለመፈናቀል የቀረቡ ተከራዮችን ጉዳይ ላይ ይመክራል፡፡ የተከራዮቹን ስም ካገኙ በኋላም በየቤታቸው በመሄድ ምን አይነት እገዛ እንደሚፈልጉ ይጠይቋቸዋል፡፡

የምህበሩ ሰብሳቢ ራሚሬዝ “ጎረቤታማቾች እርስ በርስ የሚረዳዱበትን መድረክ ለመፍጠር እንሞክራለን፡” ብለዋል፡፡

በርካታ ተከራዮች የፍርድ ቤት ቀጠሯቸውን ኦንላይን ለመከታተል የሚያስችላቸው ኢንተርኔትም ይሁን ኮምፒውተር በመኖሪያ ቤታቸው የለም፡፡ ስለዚህ የተከራዮች ማህበሩ ይህንን ጉድለት ከማሟላት በተጨማሪ በቀጠሯቸው ቀን ከጎናቸው ሆኖ ብርታት የሚሆናቸውና የብቸኝነት ስሜት እንዳይሰማቸው የሚያግዝ የማህበር አባል ይኖራል፡፡ የውድነር ተከራዮች ማህበር በተጨማሪም የህጻናት ሞግዚቶችንና የምግብ እደላ ፕሮግራሞችን እንደ አስፈላጊነቱ ያዘጋጃል ሲሎ አክለዋል ራሚሬዝ፡፡

ሌላው በዋናነት የአሜሪካ ዴሞክራቲክ ሶሻሊስት ማህበር በዲሲ የተጀመረውና ለተከራዮች ደህንነት የሚሰራውና ስቶምፕ አውት ስለምሎርድስ የተባለው ፕሮጀክት የተከራዮችን ከቤት መፈናቀል አጥብቆ የሚቃወም ሲሆን በከተማው ባሉ ህንጻዎች ላሉ ተከራዮች ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ይህ ፕሮግራም ያዘጋጀው “ጸረ መፈናቀል የስራ መምሪያ” ለተከራዮች ወሳኝ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ሲያገለግል ስለዲሲ የቤቶች ችግርም ጠቃሚ መረጃ በውስጡ ይዟል፡፡

በተጨማሪም ኢምፓወር ዲሲ የተባለው ድርጅት ከቤታቸው የመፈናቀል አደጋ የተጋረጠባቸውን ተከራዮች በመቅረብ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን የተከራዮችን መብት የሚያስረዱ ፕሮግራሞችንም ያዘጋጃል፡፡ እነሱም እንዲሁ ከቤት መፈናቀልጋ ተያይዞ ተከራዮች ያላቸውን መብት የሚያስረዳ መብትዎን ይወቁ የተባለ ጠቃሚ መረጃ ስለ መፈናቀልና የተከራይ መብቶች የሚያስረዳ ጽሁፍ አዘጋጅተዋል፡፡ እርስዎም የተከራይ ማህበር ለማቋቋም ካሰቡ ወይም ከአከራይዎትጋ በተገናኘ ድጋፍ ካስፈለገዎት እነዚህ ተቋማት ሊያግዙዎት ይችላሉ፡፡

About Author

ይህን መረጃ ለወዳጅ ዘመዶችዎ ሼር ያርጉት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *