ለአለፉት 14 አመታት ኢትዮጵያውያን ባለሞያዎችን በማገናኘት፤ እንዲሁም በርካታ መልካም አጋጣሚዎችን ለኢትዮጵያውያን ባለሞያዎች በማድረስ ከፍተኛ ሚና ሲጫወት የቆየው ዩር ኢትዮፒያን ፕሮፌሽናልስ ኔትዎርክ የተባለው ተቋም በመጪው ዲሴምበር 7 2024 ስራዎቹን ለማስተዋወቅ፤ ስኬቶቹን ለማስረዳት እንዲሁም ጎበዝ ያላቸውን ለመሸለም የእራት ፕሮግራም (ጌላ) አዘጋጅቷል።
በዚህ ፕሮግራም ላይ የመክፈቻ ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙት ዕውቁ የልብ ህክምና ባለሞያና የኸርት አታክ ኢትዮፒያ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ተስፋዬ ተሊላ ናቸው። ዶ/ር ተስፋዬ በኢትዮጵያና በዚህ በዩናይትድ ስቴትስ በርካታ የህይወት አድን ስራዎችን ሰርተዋል አሁንም በመስራት ላይ ናቸው። እስካሁንም ከ120 በላይ ህይወት አድን የልብ ቀዶ ጥገናዎችን ከማድረጋቸውም በላይ በርካቶችን በማሰልጠን የነፍስ አድን ሙያቸውን አጋርተዋል።
በተጨማሪም በዚህ ፕሮግራም ላይ ታዳጊው ሳይንቲስት ተብሎ የተሸለመው ሄማን በቀለ ምርጥ የፈጠራ ባለሞያ በመባል ሽልማት እንደሚቀበል ተነግሯል። የዝግጅቱ መድረክ በመምራት በኩል እውቋ አርቲስት ሙኒት መስፍን እንዲሁም ታዳሚውን በማዝናናት የቀድሞው የጃኖ ባንድ አባል የነበረው ዲበኩሉ ታፈሰ ይሳተፉበታል ሲሉ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።
በዚህ ፕሮግራም ላይ ታዲያ ጣፋጭ ቡፌ፤ በርካታ መጠጥ፡አጓጊ ጨረታ እንዲሁም ከሌሎች ባለሞያዎችጋ የሚገናኙበት መድረክ እንደተዘጋጀ ተናግረዋል። በዚህ ፕሮግራም ላይ መሳተፍ የፈለገ ማንኛውም ሰው ቲኬቶቹን ከዚህ ሊንክ ላይ ገዝቶ መሳተፍ ይችላል።