
የአሜሪካ ፌደራል የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ዛሬ እንዳሳወቀው ሬድ3 ተብሎ የሚጠራውን የምግብ ማቅለሚያ ለካንሰር ስለሚያጋልጥ ጥቅም ላይ እንዳይውል ከዛሬ ጃንዋሪ 15 ጀምሮ አግዷል፡፡ ይህ የምግብ ማቅለሚያ ለካንሰር ያጋልጣል ተብሎ ከ35 ዓመት በፊት በቆዳ ላይ ለሚቀቡ እንደ ሎሽንና ሊፕስቲክ ላሉ ማሳመሪያዎችና መድኃኒቶች ጥቅም ላይ እንዳይውል ተከልክሎ ነበር፡፡ ሆኖም በሲሪያል፤ በመጠጦችና በከረሜላዎች ላይ ግን ይህ ክልከላ ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቶ ዛሬ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ በተመሳሳይ በርካቶች ሌሎች ምንም የምግብነት አስተዋጾ የሌላቸው ኬሚካሎች አሁንም በምግቦች ውስጥ እንዲካተቱ የአሜሪካ ፌደራል የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ይፈቅዳል፡፡ ኢትዮጲክ ከ2 አመት በፊት በሌላ የምግብ ማቅለሚያ የሰራነው ዘገባ እንደሚያሳየው ታይታኒየም ዳዮክሳይድ የተባለውን ማቅለሚያ በመጠቀም ስኪትልስ ክስ ተመስርቶበት እንደነበረና በኋላም ይህንን ኬሚካል ከምርቶቹ እንደማያነሳ አስታውቆ እንደነበር መዘገባችን ይታወቃል፡፡
የመጪው ፕሬዘደንት ትራምፕ የጤና ቢሮ ሀላፊ እንዲሆኑ የታጩት ሮበርት ኬኔዲ በተደጋጋሚ በዚህ ጉዳይ ላይ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የቆዩ ሰው ሲሆኑ፡፡ ተሳክቶላቸው ከተሾሙ ዋና ስራቸው የሚሆነው በአገሪቱ ያለውን ስርዓተ ምግብ ማስተካከል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡