
የቨርጂንያ ገቨርነር ግሌን ያንግኪን ዛሬ ሐሙስ ፌብሯሪ 27 2025 የቨርጂንያ ስቴት ፖሊስና የማረሚያ ቤት ተቆጣጣሪዎች ከፌደራል ኢሚግሬሽን ፖሊስ ወይም አይስ (ICE) ጋር በመተባበር ወንጀለኛና ህገወጥ ያሏቸውን ስደተኞች በማሰርና ወደመጡበት በመመለስ ስራ ተባብረው እንዲሰሩ የሚያስችላቸውን ህግ ዛሬ ፈርመዋል።
በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ እንደተናገሩትም “እንደ አመራርነቴ ዋና ስራዬ የሆነውን የነዋሪዎች ደህንነት መጠበቅ በመሆኑ ይህንን ህግ በመፈረም ቨርጂንያ ከአደገኛ ወንጀለኛና ህገወጥ ስደተኞችን በማባረር የነዋሪዎችን ደህንነት እናስጠብቃለን” ብለዋል። ገቨርነሩ አክለውም “በዚህ ትዕዛዝ አማካይነት የቨርጂንያ ስቴት ፖሊሶችና የማረመያ ቤት ጠባቂዎች ከፕሬዘደንት ትራምፕ አስተዳደርጋ በመተባበር የስደተኛ ጉዳዮች ላይ ይሰራሉ፤ ወንጀለኛና አደገኛ ስደተኞችም ተመልሰው ማህበረሰቡን እንዳይቀላቀሉ ከማድረግ አልፎ ወደመጡበት አገራቸው ይላካሉ” ብለዋል።
የቨርጂንያ ሊውተናንት ገቨርነር የሆኑት ዊንሰም ኧርል-ሲርስ ሲናገሩ “እኔም ራሴ በህጋዊ መንገድ እዚህ አገር የመጣሁና አሁን ዝሜሪካዊ ዜግነቴን ያገኘሁ ስደተኛ ነኝ። ከገቨርነር ያንግኪን፤ ከጠቅላይ አቃቤ ህግጋ በመሆንም ቨርጂንያን ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን አድርገናል። ለህግ አስከባሪዎች በቂ በጀት እበመመደብ በከተሞቻችን ከባድ ወንጀሎችን ቀንሰናል። አሁን ደሞ ከፕሬዘደንት ትራምፕጋ ተባብረን በመስራት አደገኛና ነውጠኛ ህገወጥ ስደተኞችን እንቀጣለን ” ብለዋል።
የቨርጂንያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጄሰን ሚያሬዝም በበኩላቸው “ቨርጂንያውያንን ደህንነት መጠበቅ ተቀዳሚ ስራችን ነው። ይህ ዛሬ የተፈረመው ህግ በግልጽ እንዳስቀመጠው እዚህ አገር በህገወጥ መንገድ ከመጣችሁና ከባድ ወንጀል ከፈጸማችሁ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ታስራችሁ ወደመጣችሁበት ትላካላችሁ” ብለዋል።
በርካታ የስደተኛ ተንከባብካቢ ተቋማት ይህን ውሳኔ የተቃወሙ ሲሆን በተለይም የፌደራል መንግስ ከወንጀለኞችጋ አንድ ላይ ምንም ወንጀል የሌለባቸውን ስደተኞች ወደ ማጎሪያ እየከተተ በመሆኑ ይህን ህግ ተግባራዊ ማድረግ ሰብዓዊነትን መጣስ ነው ሲሉ ይከራከራሉ። ከሶስት ሳምንት በፊትበኒው ጀርሲ ከሰነድ አልባ ስደተኞችጋ አብሮ የተገኘ የአሜሪካ ዜጋ መታሰሩ በሰፊው ተዘግቧል።
ዛሬ የተፈረመውን ሙሉን ህግ ለማየት ከስር ያለውን ይጫኑ።