
የዲሲ ከንቲባ ሚውሪየል ባውዘር እንዳስታወቁት ከሆነ በዋርድ 8 ከአናኮስትያ ወንዝ በስተምስራቅ በሚገኘው የአናኮስትያ ፓርክ ውስጥ ባለውና በተልምዶ ፖፕላር ፖኢንት በሚባለው ቦታ ላይ ሊገነባ የታሰበውን ይህን የውኃ ፓርክ በአውሮፓና በዱባይ ተመሳሳይ ተቋማትን በመገንባት የሚያስተዳድረውን ተርም ግሩፕ የተባለውን ድርጅት መምረጣቸውን አስታውቀዋል።
ይህ ፕሮጀክት ለ5000 ሰዎች ጊዜያዊ የስራ ዕድል እንደሚፈጥርና ስራው ተጠናቆ ለህዝብ ክፍት ሲሆን ደሞ ለ700 ያህል ሰዎች ዘላቂ የስራ እድል እንደሚፈጥር ተነግሯል። በተጨማሪም በአናኮስትያ አካባቢ ያለውን ኢኮኖሚ እንደሚያነቃቃ ይታመናል ተብሏል።

በተጨማሪም ይህ መዝናኛ ለከተማው በአመት 27 ሚልየን ዶላር ገቢ በታክስ ያስገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል። ከንቲባዋ አክለው በአናኮስትያ አካባቢ ላሉ ነዋሪዎች የስራ እድል እንዲሁም በዲሲና አካባቢው ላሉ ሰዎች ደሞ የመዝናኛ ቦታ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ተርማ ዲሲ ግንባታው ሲጠናቀቅ ለአዋቂዎችና ለህጻናት የሚሆን የውኃ መንሸራተቻ፤ በርካታ የመዋኛ ገንዳዎች፤ እየዋኙ የሚስተናገዱባቸው ባሮች፤ የሳውናና የስቲም አገልግሎት መስቻዎችን ያካትታል ተብሏል።
በተጨማሪም ግንባታው የ70 ኤከር የወንዝ ፊለፊት ያለ ፓርክና መናፈሻ እንዲሁም 25 ኤከር ያህል ደሞ ለተለያዩ ጉዳዮች የሚውል ህንጻ እንደሚያካትት ተነግሯል።