
የ ዘ አትላንቲክ ዋና አዘጋጅ የሆነው ጄፍሪ ጎልድበርግ ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ የጦር ኃይሎች የየመን ሁውቲዎችን ከመደብደባቸው 2 ሰዓት ቀደም ብሎ ሲግናል በተባለው የመልዕክት መለዋወጫ አፕ ላይ የጦር ዝርዝሩ እንደደረሰውና መጀመሪያ ላይ ቀልድ ነው ብሎ አስቦ ነገር ግን ከ2 ሰዓት በኋላ ዜናውን ሲሰማ ቀልድ እንዳልነበር እንዳወቀ ተናግሯል።
ጄፍሪ እንደሚለው ከሆነ በቴክስት ሜሴጆቹ ላይ በግልጽምን አይነት መሳሪያዎችን እንደሚጠቀሙና በምን ሰዓት እንደሚደበድቡ ተቀምጧል። በዚህ የሜሴጅ አፕ ላይ ምክትል ፕሬዘደንት ጄዲ ቫንስ፤ የመከላከያ መሪ ፒት ሄግሴዝ፤ ስቴት ሴክረተሪ ማርኮ ሩቢዮና የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ የሆኑት ማይክል ዋልትዝ ነበረኡበት ተብሏል።
ይፋ ከሆነው የሜሴጆቹ አካል አንዱና አለም አቀፋዊ ይዘት ያለው የጄዲ ቫንስና የፒት ሄግሴዝ ምልልስ በተለይም የቀይ ባህርን ከየመን አማጽያን ቁጥጥር ውጭ በማድረግ ለንግድ መርከቦች ያለስጋት እንዲሄዱ ማድረግና ለዚህ አገልግሎታቸው ደሞ ከግብጽና ከአውሮፓ ሀገራት ክፍያ መጠየቅ እንደሚችሉ የተማከሩበት በበርካቶች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል።
በዚህ የመልዕክት ልውውጥ ወቅትም ምክትል ፕሬዘደንት ጄዲ ቫንስ “አውሮፓን በድጋሚ መታደግ አልፈልግም” ካሉ በኋላ “የሳዑዲ አረቢያን የነዳጅ አውጭ ተቋማትን ከጉዳት መከላከል አለብን ” ያሉ ሲሆን ፒት ሄግሴዝም “የአውሮፓውያንን ተመጽዋችነት መጥላትህን እጋራለው ብለው መልሰውላቸዋል።”
የመከላከያው መሪ ፒት ሄግሴዝ ዜናውን ሙሉ ለሙሉ ሀሰት ነው ሲሉ ለጋዜጠኞች መልስ ሰጥተዋል።
በጉዳዩ ላይ የተጠየቁት የዋይት ኃውስ ሰዎች ዜናው እውነት እንደሆነ አረጋግጠዋል። የዴሞክራት ፓርቲ አባላትም በርካታ ሂሶችን ሰተዋል። በተለይም የሲግናል አፕ ለእንደዚህ ያለ የአገር ደህንነት ጉዳይ መዋል የለበትም በሚል በርካቶች ምርመራ እንዲደረግ ጠርተዋል።