@ethiopique202 (23)

ፕሬዘደንት ትራምፕ ከሰሞኑ በፈረሙት የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝና በወሰኑት ውሳኔ በተለይም በአሜሪካ በተለያየ ደረጃ በሚገኙ ስደተኞች ዘንድ ዘላቂ ተጽዕኖ ሊያደርሱ የሚችሉ ውሳኔዎችን ወስነዋል። በበርካታ የሲቪል መብት ተሟጋቾችና በህገ መንግስት ባለሞያዎች ዘንድም እኚህ ሁለት እርምጃዎች ተወቅሰዋል። አንደኛው ትዕዛዝ በአሜሪካ በጊዜያዊነት የህግ ከለላ(ቲ ፒ ኤስ) ጥላ ስር የነበሩ ከ500 ሺህ በላይ የኩባ፤ ሄይቲ፤ ኒካራጓና ቬንዙዌላ አገር ዜጎችን የህግ ከለላ በማንሳት ወደ ዲፖርቴሽን ሂደት እንዲገቡ አድርጓል።

የዩናይትድ ስቴትስ ዲፓርትመንት ኦፍ ጀስቲስ (ፍትህ ዲፓርትመንት) እንዳስታወቀው በነዚህ አገራት ከዚህ ቀደም የነበረውና አስቸኳይ የነበረው የሰብዓዊ ቀውስ ባለመኖሩ ይህንን ህጋዊ ከለላ አስጠብቆ መቆየቱ አስፈላጊ እንዳልሆነ አስረድተዋል። ይህንን ተከትሎም የስደተኛ ደንብ አስከባሪዎች (ICE) በቀጣይ ወራት ይህንን ህግ ተግባራዊ ለማድረግ ወደ ስራ እንደሚገቡና በርካታ ሰዎች ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠበቃል ተብሏል።

ሁለተኛውና ቅዳሜ ማርች 22 የተፈረመው የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ደሞ በዩናይትድ ስቴትስ ህጋዊ ፈቃድ ኖሯቸው የህግ ማማከርና የጥብቅና አገልግሎት በሚሰጡ ሰዎችና ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ትዕዛዝ ሲሆን በዚህ ትዕዛዝ በተለይም ለስደተኞች የጥብቅና አገልግሎት የሚሰጡ የህግ ባለሞያዎች ደንበኞቻቸውን የአሜሪካንን ህግ እንዲያታልሉ በመምከርና የህግ ስርዓቱን በማጭበርበር፤ እንዲሁም የፌደራል መንግስትን በስደተኛ ጉዳዮች፤ በምርጫና በአገር ደህንነት ጉዳዮች በፍርድ ቤት በመክሰስ ያስቸገሩ ያላቸውን ጠበቆችና የህግ ድርጅቶች በስም በመጥቀስ ምርመራ እንዲደረግባቸውና ጥፋተኛ የተባሉት እንዲቀጡ አመራር ተሰቷል።

በዚህ አዲስ ህግ መሰረትም ላለፉት 8 አመታት ከላይ በተጠቀሱት ተግባራት ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ የህግ ባለሞያዎች ላይ ምርመራ እንዲደረግና እርምጃ እንዲወሰድባቸው ይጠይቃል። በርካቶች ታዲያ ይሄ እርምጃ ፖለቲካዊ አላማ ያለውና የህግ ባለሞያዎችን እጅ በመጠምዘዝ ለስደተኞች እንዳይቆሙ፤ መንግስትንም ሲሳሳት እንዳይጠይቁ ለማፈን የተደረገ ነው ሲሉ ይስተዋላሉ። የትራምፕ አስተዳደር በበኩሉ ይህ እርምጃ የፍትህ አካላት ላይ የሚታየውን የእምነት መሸርሸር ለመታደግ የተደረግ እርምጃ ነው ይላል።

ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ታዲያ ፕሬዘደንት ትራምፕ በማርች 15 2025 ባወጁት 200 አመታትን ባስቆጠረውና በ1798 በተረቀቀው የኤልየን ኢነሚስ አክት (የውጭ ጠላቶች ህግ) በመጥቀስና ወደ ተግባር እንዲገባ በማድረግ የቬንዙዌላ ጋንግ አባላትን በጠላትነት በመፈረጅ የተወሰኑ ቬኑዜላውያንን ህገመንግስቱ ለሌሎች የሚፈቅደውን በፍርድ ቤት የመዳኘት መብትን በመግፈፍ ወደ ኤልሳልቫዶር ጠርዘው ልከዋቸዋል።

ይህ ከመሆኑ በፊትም የፌደራል ዳኛ የሆኑት ቦዝበርግ በጊዜያዊነት ይህ ህግ ተግባራዊ እንዳይሆን አግደው የነበረ ቢሆንም ፕሬዘደንት ትራምፕ ግን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሲደረግ ታሳሪዎቹ ከአገር ውጭ እንደነበሩና በነሱ ላይ ተፈጻሚ ሊሆን እንደማይችል ይከራከራሉ።

በርካታ የሲቪል መብት ተክራካሪዎችና የተባረሩት ሰዎች ቤተሰቦች እንደሚሉ ከተባረሩት ውስጥ የተወሰኑት ከተጠቀሰው ጋንግ (የወንጀል ቡድን)ጋ ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ከተባረሩት መኃከል አንደኛው ጀርሲ ሪየስ ባሪዮስ የተባለ የ36 አመት ወጣት ሲሆን በ2024 በህጋዊ መንገድ ወደ አሜሪካ መቶ የአሳይለም ጥገኝነት ጠይቆ ምላሽ እየተጠባበቀ የነበረ የቬንዙዌላ ፕሮፌሽናል ኳስ ተጫዋች እንደሆነና ለዚህ እንዲበቃ ያደረገው እጁ ላይ ያለው ንቅሳት የወንጀል ቡድኑ አባላት ያላቸው አይነት ንቅሳት ነው በሚል ታፍሶ እንደተባረረ ተነግሯል።

የሲቪል መብት ተከራካሪዎቹ እንደሚሉት ደሞ የዚህ ሰው እጅ ላይ ያለው ንቅሳት የሪያል ማድሪድ ክለብ ሎጎ እንደሆነ ተናግረዋል።

የፕሬዘደንት ትራምፕ አስተዳደር ሰኞ ማርች 24 ይህንን የፍርድ እግድ እንዲነሳለት ባቀረበው የይግባኝ ጥያቄን የሰሙት ዳኛ በበኩላቸው “ከሰሞኑ የቬንዙዌላ ዜጋ ተባራሪዎች ይልቅ በ2ኛው የአለም ጦርነት ወቅት የተያዙ የጀርመን ናዚዎች ራሳቸውን ከዲፖርቴሽን እንዲከላከሉና መብታቸውን እንዲያስከብሩ የተሻለ ዕድል ነበራቸው” ብለዋል።

About Author

ይህን መረጃ ለወዳጅ ዘመዶችዎ ሼር ያርጉት

Sign In

Register

Reset Password

Please enter your username or email address, you will receive a link to create a new password via email.