@ethiopique202 (72)

ኢትዮጲክ – ከኢትዮጲክ ጋር ስለሚኖርሽ ቆይታ እያመሰገንን፤ በቅድሚያ እስቲ እራስሽን አስተዋውቂልን።

ራኬብ – እሺ እኔም ይሄንን ዕድል ስለሰጣችሁኝ እና ኢንተርቪው ስላደረጋችሁኝ በጣም አመሰግናለሁ። ስሜ ራኬብ ዘለቀ እባላለሁ። ተወልጄ ያደኩት አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ነው። ወደዚህ ሀገር መጥቼ ትምህርት ቤት ገብቼ ከሆዋርድ ዩኒቨርስቲ በሜዲካል ቴክኖሎጂ ዲግሪ ይዣለሁ። እሳካሁንም በተለያዩ ሆስፒታሎች ውስጥ እየሰራሁኝ ነው። ሁለት ልጆች አሉኝ። ኢቴል እና የአርሴማ ግሩም ይባላሉ። እንግዲህ ይሄው ነው።

ኢትዮጲክ – የኔታ የቋንቋ እና የባህል ተቋም እንዴት እና መቼ ነው የተመሰረተው? ጥቂት ስለ አጀማመሩ ብትነግሪን?

ራኬብ – ያው የኔታ የተመሰረተው በቅርብ ጊዜ ነው። ግን መጀመሪያም ይሄንን ትምህርትቤት ከመክፈቴ በፊት ሌላ ቢዝነስ ውስጥ ነበርኩኝ። ያ ቢዝነስ ነው እንግዲህ ይሄ ት/ቤት እንዲከፈት ምክንያት የሆነው። ልጄ ሦስት ዓመቷ እያለ የተለያዩ ፊደሎችን እንዲሁም ባህሏን እንድታውቅ ማቴሪያሎችን በምፈልግበት ሰዓት፤ በወቅቱ ብዙም አማራጭ አልነበረም። ስለዚህ እስቲ የራሴ የሆነ ነገር ልሞክር ብዬ ልጄ ፐዝል ትወድ ስለነበረ፣ ፐዝል መስራት ጀመርኩኝ ማለት ነው። ሀሁን በፐዝል እየተጫወተች በቀላሉ መንገድ እንድታውቅ ለማድረግ ነበር ዓላማዬ። እንደሚታወቀው ፊደላችን ብዙ ስለሆነ ሁሉንም ነገር መሸምደድ ከባድ ነው። በተለይ እዚህ ሀገር ደግሞ ሁሉንም ነገር በቀላሉ ስለሆነ የሚያስተምሯቸው ከእነሱ ጋር በቀላሉ መንገድ አብረን መራመድ አለብን፤ ስለዚህ በዛ ነበር የጀምርኩት። እና ከጊዜ በኋላ እየጨመርኩኝ፤ ታሪክ አክሱም ላሊበላ እንዴት ነው የምናስተምራቸው እያልኩ በፐዝል መልክ እየተጫወቱ እንዲማሩ ያንን ሰራሁ እንዲሁም ድምጽ ያላቸው የምስል ካርዶች(ፍላሽ ካርድ) አደረግን ያንን በኦን ላየን እና ቲክቶክ ላይ እንሸጣለን።… ከዛ ተነስቼ ነው እንግዲህ ወደ ትምህርት ቤቱ የመጣሁት ማለት ነው።

Image: Provided

ኢትዮጲክ – ምን ነበር ትምህርት ቤት ያስፈልጋል ብሎ ያስወሰነሽ?

ራኬብ – ክፍተቱን እራሴ እየሁት። ይሄንን ነገር ስሰራ ብዙ ጊዜ ከወላጆች ጋር ነው የምገናኘው እና፤ ወላጆች ደግሞ በእንግሊዘኛ መግባባቱንም ቢችሉት እንኳን እዚህ ሀገር ተወልደው ካላደጉ የባህል እና የትምህርት አሰጣጡ ላይ ክፍተት አለባቸው። ስለዚህ ለምንድነው ይሄንን ነገር ወደ ትምህርት ቤት አሳድጌ ቤተሰብም በአፍ መፍቻ ቋንቋው ከልጆቹ ጋር እንዲግባባባ፣ ልጆቹም በራስ መተማመን ኖሯቸው መልስ መስጠት እንዲችሉ የማላደርገው በሚል ነው ትምህርት ቤቱን የከፈትኩት።

ኢትዮጲክ– በትምህርት ቤት ውስጥ ምን ዓይነት መርሃግብሮች አሏችሁ?

ራኬብ – ት/ቤቱ ከተከፈተ እንግዲህ አንድ ዓመት ሆኖታል። 45 ተማሪዎች አሉን። በኦንላየን እና በአካል ነው ትምህርቱ የሚሰጠው። ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ድረስ ክፍት ነው። ከሰኞ እስከ አርብ ያሉት ፕሮግራሞቻችን ከ 5፡00 ፒኤም በኋላ ናቸው። ምክንያቱም ቀን ላይ ልጆቹ ትምህርት ቤት ይሆናሉ በሚል ነው። አሁን ላይ በዋናነት የምናስተምረው አማርኛ ነው። ነገር ግን ከፊታችን ነሃሴ ወር ጀምሮ የትግረኛ እና የኦሮምኛ ቋንቋዎችንም ማስተማር እንጀምራለን። ሦስት ዓይነት ቋንቋ ይኖረናል ማለት ነው። ሀሳባችን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነገሩ ቋንቋዎችን እየጨመሩ መሄድ ነው።

ኢትዮጲክ – በዋናነት በዚህ ሥራ ላይ ያስተዋልሽው የቋንቋ እና የባህል ክፍተት ምን ይመስላል?

ራኬብ -እኔ እንግዲህ እስካሁን ባየሁት ትልቁ ክፍተት ያለው ወላጅ ጋር ነው። ምክንያቱም ቤተሰብ ይሮጣል ሥራ አለ ሌሎችም ነገሮች አሉ እና ልጆች በእንግሊዘኛ ሲመልሱ በአማርኛ እያስተካከሉ ያለመታከት መከታተል ይከብዳቸዋል። ነገር ግን እኔ ወላጆችን የምመክረው ቋንቋ የሚጠፋ ነገር ነው ስለዚህ በተቻለ መጠን በቻላችሁት እና ባገኛችሁት ሰዓት ሁሉ አፋቸው እንዲለምድ ዕድሉን ለልጆች ስጡ ነው። የእኛ ችግር ምንድነው? ልጆቹን ስለምናውቃቸው ተናግረው ሳይጨርሱ ቶሎ ገብቶን እናደርገዋለን። ነገር ግን ልጆቹ ሀሳባቸውን በአማርኛ ተናግረው እስኪጨርሱ መጠበቅ ያስፈልጋል። እንዲሞክሩ ዕድል መስጠት ያስፈልጋል። ጥናቶችም የሚያሳዩት ከአንድ በላይ ቋንቋ መናገር ለልጆች አዕምሮ ጠቃሚ መሆኑን ነው። …

ኢትዮጲክ – የኔታ እጅግ ብዙ የሀበሻ ማኅበረሰብ በሚገኝበት በሜሪላንድ ሞንጎሞሪ ካውንቲ ውስጥ ነው የሚገኘው። አንቺም ከካውንቲው ጋር በቅርበት ድጋፍ አግኝተሽ እየሰራሽ ነው። ምን ዓይነት ድጋፍ ነው ያገኘሽው? ልምድሽስ ምን ይመስላል?

ራኬብ – በጣም ደስ የሚል ነው። የአድናቆት እና የእውቅና ደብዳቤ ከካውንቲው ፕሬዝዳንት ማርክ ኢልሪች በቅርቡ ተደርጎልናል። እንግዲህ ይሄንን ያገኘነው በምርጫ ተመርጠን ነው። የሆነ ነገር ስትሰራ ከኋላ የሚያይ ሰው አለ። እኛ ከማኅበረሰቡ እንዲሁም ከልጆች ጋር እየሰራን ነው። ያንን በአካልም መጥተው በማየት ከዚህ በኋላ ዓላማችሁ ምንድነው በምን እናግዛችሁ? ብለው ጠይቀውናል። ቅድም ሳልናገር ያለፍኩት በየኔታ ማሲንቆ፣ በገና ክራር እንዲሁም ፒያኖ እና ጊታር የሙዚቃ መሳሪያ ትምህርቶችንም እንሰጣለን። ይሄ የካውንቲውን ፕሬዝዳንት በጣም አስደስቷቸው ነበር። እነዚህ ለኢትዮጵያውያን ብቻም ሳይሆን ማንም መጥቶ መማር የሚችላቸው ነገሮች ናቸው። በዛ ላይ ብዙ ነገሮችን አውርተናል። ይሄ እውቅናም እንደ የኔታ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያም አንድ እርምጃ እንደተራመድን ታውቆ በካውንቲው መሰጠቱ ትልቅ ነገር ነው ብዬ አስባለሁ።

ኢትዮጲክ – እንደአንቺ ሁሉ አዲስ ለሆኑ ንግድም ሆነ የተለያዩ ሥራዎችን መጀመር ለሚፈልጉ ሰዎች ምን ትመክሪያለሽ?

ራኬብ – እኔ የምለው ሁሌም ቢሆን የሰው ልጅ ውስጡን ያዳምጥ ነው። ለገንዘብ ብቻ ሳይሆን የሚወዱትንም ነገር ነው መስራት ያለባቸው። ለገንዘቡ ተብሎ የሚደረግ ነገር ሁልጊዜ የሆነ ቦታ ላይ ገንዘቡ ሲቆም ይቆማል። እኔ ይሄንን ነገር ስጀምረው ፓሽኑ (ፍቅሩ) ነበረኝ። አንድ ሥራ ሲጀመር ይሄ ነገር ይሆነኛል ወይ? እችለዋለሁ ወይ? ማለት ያስፈልጋል። ሁለተኛው ነገር ደግሞ ከሌሎች ማኅበረሰቦች እና ድርጅቶች ጋርም መተባበር ያስፈልጋል። አሁን እኛ ከሞንጎሞሪ ኮሌጅ ጋር አብረን ልንሰራ ነው። ትንሽ የወረቀት ሥራዎች ናቸው የቀሩን እንጂ ፓርትነር ልናደርግ ነው። እነዚህ የመሰሉ አጋጣሚዎችን ሲመጡ መጠቀም ያስፈልጋል። እኛ አሁን በማኅበረሰብ ደረጃ እንደስፓኒሽ ሁሉ አማርኛም መሰጠት አለበት፣ እንዴት ነው ክሬዲት እንዲያዝለትስ የሚደረገው በሚለው ላይ እየሰራን ነው። በእርግጥ በሀዋርድ ዩኒቨርስቲ ውስጥም አማርኛ ቋንቋ ትምህርት ይሰጣል። ነገር ግን በሃይ ስኩል እና በዩኒቨርስቲም መሰጠት አለበት በሚለው ላይም እያወራን ነው። እስኪ ወደፊት የሚሆነውን እናያለን።

ኢትዮጲክ – የወደፊት ህልም እና ዕቅዶቻችሁስ ምን ይመስላሉ?

ራኬብ – አሁን በቅርቡ ት/ቤት ሲዘጋ ሰመር ካምፓችን (የበጋ መቆያችን) ይከፈታል። እ.ኤ.አ ከሰኔ 30 እስከ ነሃሴ አንድ ድረስ ለአምስት ሳምንታት ነው የሚቆየው። እዚህ ሀገር ካለው ሰመር ካምፕ የተለየ ነው። የምናተኩረው አማርኛ ትምህርት እንዲሁም ደግሞ የእኛን ባህል የሚያንጸባርቁ ነገሮች ላይ ነው። ጥጥ መፍተል፣ ገበጣ፣ ዳማ የመሳሰሉትን እኛ ያደግንባቸውን ነገሮች እንዲረዱ እና እንዲያውቁ የሚያደርጉ የተለያዩ አክቲቪቲዎች (እንቅስቃሴዎች) አሉ።
ሀበሻ ብቻ ሳይሆን የዚህ ሀገርም ማንኛውም ሰው መመዝገብ እና መማር ይችላል። እኛ ጭቃ እንዳቦካነው ጭቃ እያቦኩ፣ ጀበና እየሰሩ እንዲማሩና እንዲደሰቱ ተዘጋጅተናል። ከዛ ውጭ ደግሞ የቀጣይ ዓመት ትምህርት የፊታችን ነሃሴ ይጀምራል። ያለን ቦታ በጣም ውስን ነው። ሰው ከበዛ ዌቲንግ ሊስት (ተጠባባቂ) እንዲሆኑ ነው የምንደርገው። ስለዚህ መመዝገብ የሚፈልጉ ሰዎች አስበውበት በጊዜ ቢመዘገቡ እላለሁ።

ኢትዮጲክ – ራኬብ ዘለቀ ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።

ራኬብ -እኔም ይሄንን ዕድል ስለሰጣችሁኝ፤በጣም አመሰግናለሁ፤ እግዚአብሔር ይሥጥልኝ።

About Author

ይህን መረጃ ለወዳጅ ዘመዶችዎ ሼር ያርጉት

Sign In

Register

Reset Password

Please enter your username or email address, you will receive a link to create a new password via email.