በ2023 በርካታ ኢትዮጵያውያንን ከወትሮው ባልተለመደ መልኩ በአሜሪካ በሚኖሩበት አካባቢ ባሉ ፖሊሲዎች ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለማሰማትና መብታቸውን ለማስከበር እንዲሁም ድምጻቸውን ለማሰማት የተሳተፉበትና አገር አቀፍ የሚድያ ሽፋን ያገኘው የሞንጎምሪ ካውንቲ ስርዓተ ትምህርት ፖሊሲን በበላይነት የሚያስተዳድረው የትምህርት ቦርድ ለ2024 ሶስት መቀመጫዎቹ ለምርጫ ይቀርባሉ።
የዚህ ቦርድ የመጀመሪያ (ፕራይመሪ) ምርጫ ሜይ 14፣ 2024 የሚከናወን ሲሆን በዚህ የፕራይመሪ ምርጫ ከፍተኛ ድምጽ ያገኙ 2 ተመራጮች ወደ ዋናው የኖቨምበር ምርጫ ይሸጋገራሉ።
በዚህ ምርጫ እንወዳደራለን ያሉ 14 ተመራጮች የተመዘገቡ ሲሆን የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን ጀምረዋል። ከነዚህም ውስት ሶስቱ አሁን በቦርድ አባልነት እያገለገሉ ያሉት ቫይስ ፕሬዘደንቷ ሊን ኃሪስ፤ የዲስትሪክት 2 ተወካዩአ ሬቤካ ስሞንድሮውስኪና ሼብራ ኤቫንስ ይገኙበታል።
ማስታወቂያ:- በየጊዜው የምናወጣቸውን መረጃዎች ለማግኘት በፌስቡክና … በቴሌግራም ይከታተሉ:: ለወዳጅ ጏደኞችም ይንገሯቸው::
በዘንድሮው የትምህርት ቦርድ ምርጫ የሚደረግባቸው ሶስት መቀመጫዎች የዋናው ቦርድ (AT-Large), የዲስትሪክት 2 መቀመጫና የዲስትሪክት 4 መቀመጫዎች ናቸው። ማንኛውም የካውንቲው ነዋሪ በዋናው ቦርድ (At-LArge) ምርጫ ላይ መሳተፍ የሚችል ሲሆን የዲስትሪክት 2ና 4 ላይ ለመሳተፍ ግን የዛ ዲስትሪክት ነዋሪ መሆንን ይጠይቃል። (ካርታውን ይመልከቱ)
በዘንድሮው ትምህርት ቦርድ ምርጫ በባለስልጣናቱ ተፈጽመዋል የተባሉ ወሲባዊ ጥቃቶችና ሌሎች የህግ ጥሰቶች በአንድ ወገን ሲኖሩ በሌላ ወገን ደሞ ወላጆች በልጆቻቸው ትምህርት በተለይም ከባህልና ከኃይማኖትጋ የሚጋጩ ትምህርቶችን ወላጆች ልጆቻቸው እንዳይሳተፉ ከፈለጉ የሚፈቅድ ህግ እንዲረቀቅ በሚደግፉና በሚቃወሙ መኃከል ፍጥጫ እንደሚኖር ይጠበቃል።
በዚህ ምርጫ የሚወዳደሩት ተፎካካሪዎች የሚከተሉት ናቸው።
በዋና ቦርድ (At-LArge) አባልነት ለመወዳደር
- ሊን ኃሪስ
- ሻሪፍ ሂዳያት
- መሊሳ ኪም
- ጆናታን ሎንግ
- ፊትዝጀርላንድ ሞፈር
- ሪታ ሞንቶያ
ለዲስትሪክት 2 የሚወዳደሩ
- ብሬንዳ ኤም. ዲያዝ
- ሪኪ ፋዬ ሙዪ
- ሬቤካ ኬለር ስሞንድሮውስኪ
- አቢ ቲዎዬ
- ናታሊ ዚመርማን
ለዲስትሪክት 4 የሚወዳደሩ
- ሼብራ ኤቫንስ
- ቤታኒ ኤስ ሜንድል
- ሎውራ ኤም ስቴዋርት
ይህ ምርጫ ከባድ ፉክክር የሚኖርበት እንደሆነ ይጠበቃል። በ2022 በተደረገው ምርጫ የካውንቲው ኤክስኪውቲቭ ማርክ ኤልሪች ተቀናቃኛቸውን በ 36 ድምጽ ብቻ አሸንፈው ነው ስልጣን የያዙት። ይህ የሚያሳየው የእያንዳንዱ ሰው ድምጽ በካውንቲው ዋጋ እንዳለው ነው።
የኢትዮጲክ ባልደረቦች የእነዚህን ተወዳዳሪዎች አቋም ለመጠየቅና መራጭች ከመምረጣቸው በፊት በቂ መረጃ እንዲኖራቸው ለማገዝ አቅደዋል። እርስዎ እኚህን ተመራጮች እንድንጠይቅልዎ የምትፈልጉት ጥያቄ ካለ እስከ ረቡዕ ማርች 13 እስከ 5pm በዚህ ሊንክ በመጠቀም ወይንም በኢሜይላችን admin@ethiopique.com ወይም በቴክስት ወይም በቮይስሜይል (202)-361-6295 ይላኩልን። በተጨማሪም ከስር ያለውን መጠይቅ በመሙላት ኃሳብዎን ያጋሩን፡፡ እናመሰግናለን፡፡