ለጥቆማው አማን ወዲፖስታን እናመሰግናለን
የአዲሱ አመት መጀመርን አስመልክቶ አዳዲስ ህጎች በተለያዩ አካባቢዎች ተግባራዊ ይሆናሉ። አንዳንዶቹ ህጎች ልክ አመቱ ሲጀምር ጃንዋሪ 1 የሚጀምሩ ሲሆን የተወሰኑት ደሞ ቀስ ብለው ከወራትና ሳምንታት በኋላ ይጀምራሉ። እነዚህ ህጎች የሚከተሉት ናቸው።
ቀይ የትራፊክ መብራት ላይ ወደቀኝ መታጠፍ
በ2022 ደህንነታቸው የተጠበቁ መንገዶችን ለማረጋገጥ በወጣው ህግ መሰረት ከጃንዋሪ 1 2025 ጀምሮ በዋሽንግተን ዲሲ ባሉ መንገዶች ላይ ወደቀኝ መታጠፍን የሚፈቅድ ታፔላ ካልተለጠፈ በስተቀር በቀይ መብራት ከተያዙ ወደቀኝ መታጠፍ አይችሉም።
ይህንን ህግ ተግባራዊ ለማድረግና ደንብ ለማስክከበር ተብሉ የተጠየቀው የ385ሺ ዶላር በጀት ታዲያ በኮንግረስ ባለመፈቀዱ በከተማው ካሉት የ1600 ያህል ቅያሶች በግማሾቹ ብቻ ነው ከተማው ደንብ ማስከበር የሚችለው።
ለነፍሰጡሮች የቤት ጉብኝት በኢንሹራንስ እንዲከፈል
በዋሽንግተን ዲሲ ላሉ ነፍሰጡሮች በየቤታቸው እየሄዱ ትምህርትና ስልጠና እንዲሁም የማማከር አገልግሎት የሚሰጡ 17 ያህል ፕሮግራሞች አሉ። እነዚህ ፕሮግራሞች እስካሁን ክፍያቸውን የሚያገኙት ከከተማውና ከፌደራል በጀት ነበር። ከመጪው አዲስ አመት ጀምሮ ግን በዲሲ ሄልዝኬር አሊያንስ፤ በሜዲኬይድ ወይም በኢሚግራንት ችልድረንስ ፕሮግራም የታቀፉ ቤተሰቦችን ክፍያ ኢንሹራንሳቸው ራሱ ይከፍለዋል።
ከቦታ ቦታ የሚጓጓዙ የዱር እንስሳ ጥበቃ ደንብ
ይህ ደንብ ከማርች 2023 ጀምሮ ህግ ሆኖ የጸደቀ ሲሆን ከመጪው አዲስ አመት ጀምሮ ማንኛውም በከተማው አዲስ ቤት የሚሰራ ወይንም የቤቱን ውጫዊ አካል የሚያሳድስ ሰው ለወፎች ተስማሚ የሆነ ቁስ እንዲጠቀም ያዛል።
የመጀመሪያ ጊዜ ቤት ገዢዎች
ከ2025 ጀምሮ የመጀመሪያ ጊዜ ቤት ገዢዎች የታክስ ጥቅም ለማግኘት የሚገዙት ቤት ዋጋ ከ753ሺ ዶላር መብለጥ የለበትም።
የታክስ አሰባሰብ ለውጦች
በኦክቶበር 2025 ጀምሮ ከዚህ ቀደም 6% የነበረው የአገልግሎት ታክስ ወደ 6.5% ያድጋል። ለኤሌክትሪክ መኪኖች ተደርጎ የነበረው የኤክሳይዝ ታክስ ምህረት ይነሳል። እንዲሁም በጋዝ ለሚሰሩ መኪኖች የኤክሳይዝ ታክስ መጠኑ ይጨምራል።