
በኒው ዮርክ ከተማ በታችኛው የማንሀታን ክፍል ባለው የብሮድዌይ ጎዳና ላይ ወደ 200 የሚጠጉ ታሪካዊ ጀግኖችን የሚዘክሩ የጎዳና ሰልፎች ተከናውነዋል።
በነዚህ በዓላት ወቅት ታዲያ የከተማው ህዝብና የትርዒቱ ታዳሚ ከዳር ቆሞ ወይንም ሰልፉ ከሚደረግበት መንገድ ግራና ቀኝ ሆነው የተጠቀለለ ወረቀት ወይን ሶፍት በመወርወር ደስታቸውንና ድጋፋቸውን የሚገልጹበት በዓል ሲሆን በአገሬውም የቲከር-ቴፕ ፐሬድ (ticker-tape parades) በመባል ይታወቃል።
እኚህ ጥቅልል ወረቀቶች ቀደም ባሉት ጊዜያት የስቶክ ማርኬት የሚገበያዩበት ተቋም ውስጥ የገበያ ዋጋ የሚያሳየው ማሽን ውስጥ የምትገባ ወረቀት ነበረች፤፡
በኒው ዮርክ የሚደረገው ይህ የጎዳና ሰልፍ ትርዒት ካናየን ኦፍ ሂሮስ (Canyon of Heroes) በመባል ይታወቃል። በዚህ ትርዒት ላይም የጦር ጀግኖች፤ ወደስፔስ የሔዱ ጠፈርተኞች፤ በርካታ የአሜሪካና የሌላ አገራት ፕሬዘደንቶች፤ ይሞገሱብታል።
የመጀመሪያው የቲከር ቴፕ የጎዳና ላይ ትርዒት የተከናወነው በ1886 ሲሆን ይህም የነጻነት ምልክት የሆነውን የስታቹ ኦፍ ሊበርቲን ለማሰብ የተዘጋጀ ሰልፍ ነበር።

ከዛ በኋላ በየዘመኑ በርካታ ታዋቂ ሰዎች ጀግና ተብለው በዚህ ጎዳና ላይ ህዝብ በተሰበሰበበት ትርዒት አሳይተዋል።
ከነዚህም ተጠቃሾቹ የአፖሎ 11 ጠፈርተኞች፤ ኔልሰን ማንዴላ፤ ዊንስተን ቸርችል፤ ቻርለስ ደጎል፤ ጆን ኤፍ ኬኔዲና ድዋይት አይዘን ሀወር ተጠቃሽ ናቸው። የነዚህ ሁሉ ሰዎች ስም በመታሰቢያ መልክ በኒው ዮርክ ታችኛው ማንሀታን በሚገኘው የብሮድዌይ ጎዳና ላይ ተተይቦ ይታያል። በዚህ ጎዳና ላይ ስማቸው የተተየበላቸውን ሰዎች ዝርዝር ዊኪፒዲያ ላይ ማየት ይችላሉ።
ከነዚህ ሁሉ መኃልም የቀድሞው የኢትዮጵያው ንጉስ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ አንዱ ናቸው።

የኢትዮጵያው ንጉስ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በወቅቱ ስለነበራቸው ስለ ጉዟቸውና ስለ ኒው ዮርክ ቆይታቸው የሚያሳየውን የጆን ኤፍ ኬኔዲ ላይብረሪ ያዘጋጀውን ቪዲዮ እነሆ።