
ሰኞ ማርች 24 የዲሲ ካውንስል የፍትህና የህዝብ ደህንነት ኮሚቴ ዋና ሊቀ መንበር የሆኑት ብሩክ ፒንቶ ይፋ ባደረጉት ፒስ ዲሲ በተባለ ረቂቅ የህግ ማዕቀፍ አስተዋውቀዋል፡፡ በዚህ ሁለገብ የህግ ማዕቀፍ መሰረትም በዋሽንግተን ዲሲ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት አይነተኛ ሚና ይጫወታሉ የትባሉ ተግባራት ተካተዋል፡፡ ከነዚህ ተግባራት መሀከል በዋናነት የከተማዋን ታዳጊዎች ማነቃቃት፤ ሁከትን መከላከል፤ የህዝብ ደህንነት ስራዎች ድጋፍ እና ከማረሚያ ቤት ተመላሽ የሚሆኑ ዜጎች ድጋፍ ማዘጋጀት ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪ በትምህርት ተቋማት የደህንነት ስራዎች እንዲበረታቱ፤ የሁከትን መከላከል ስራዎች እንዲሳለጡ፤ የህግ አስከባሪ አካላት ስራቸውን እንዳይለቁ የሚያግዙ እርምጃዎችና ከዚህ ቀደም ታስረው ለተፈቱ ግለሰቦች የመኖሪያ ቤትና የስራ እድል እንዲፈጠር ያግዛል ተብሏል፡፡ ይህ ፒስ ዲሲ የተባለው አዲስ ረቂቅ ባለፈው አመት ሴኪውር ዲሲ ተብሎ ከወጣውና በከተማው የተሻለ ደህንነትን ያሳየው ህግ ተከታይ ሆኖ እንደሚያገለግል ተነግሯል፡፡