
ፕሬዘደንት ትራምፕ ዛሬ ሰኞ ኤፕሪል 28 ይፈርሙታል በተባለው ኤክሲኪውቲቭ ኦርደር ላይ ማንኛውም የንግድ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች (commercial truck drivers) የማሽከርከር ፈቃድ ከማግኘታቸው በፊት የእንግሊዝኛ ቋንቋ መቻላቸው መረጋገጥ እንዳለበት ያዛል፡፡
በዚህ ትዕዛዝ መሰረትም የፌደራል ትራንፖርት ባለስልጣን የአሽከርካሪዎችን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቃት እንዲፈትንና የከባድ መኪና ማሽከርከሪያ ፍቃድን (CDL) ላይ ማሻሻያ እንዲያደርግ እንደሚያዝ የዋይት ሀውስ ፕሬስ ሴክረተሪ ካሮሊን ሌቪት በትዊተር ባጋራችው የብሪይትባርት ድረገጽ ላይ ተጠቁሟል፡፡
የትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ሃላፊ የሆኑት ሾን ደፊም በበኩላቸው በትዊተር አካውንታቸው እንዳስታወቁት ዛሬ ከፕሬዘደትን ትራምፕጋ ትልቅ ዜና እንደሚለቁና ይህም ዜና የአሜሪካ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና አሜሪካውኛን የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ቅድሚያ እንዲሰለፉ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
በኤፕሪል 10 የዋዮሚንግ የሪፐብሊካን ተወካይ የሆኑት ሄግማን ለሻን ደፊ በላኩት ደብዳቤ በኦባማ አስተዳደር ወቅት እንዲቀር የተደረቀው የእንግሊዝኛ ቋንቋ መስፈርት እንዲመለስ እንደጠየቁና ከዚህ ከኦባማ ውሳኔ በኋላ ቋንቋ በማይችሉ አሽከርካሪዎች በርካታ አደጋዎች እንደደረሱ ተናግረዋል፡፡
የዚህ ህግ ደጋፊዎች አችከርካሪዎች በአገሪቱ ያሉ የመንገድ ምልክቶችንና ሌሎች መረጃዎችን ለመረዳት እንግሊዝኛ ወሳኝ በመሆኑ ጉዳዩ ለድርድር ራሱ መቅረብ እንደሌለበት ያስረዳሉ፡፡ እንደ ኦክላሆማ ባሉ ስቴቶች ይህ ጉዳይ ህግ ሆኖ ለመጽደቅ ረቂቁ በስቴቱ የተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡