
በሜሪላንድ መወሰኛ ምክር ቤት ከሰሞኑ በጸደቀው ህግ መሰረት በሜሪላንድ ያሉ ካውንቲዎች የታክስ መጠናቸውን እስከ 3.3% እንዲያሳድጉ መፍቀዱን ተከትሎ የሞንጎምሪ ካንውቲ ኤክስኪውቲቭ የሆኑት ማርክ ኤልሪች አስቀድመው በቤት ባለቤቶች ላይ ሊጥሉት ያሰቡትን የ3.4% ታክስ አስቀርተው በጠቅላላው ህዝብ ላይ ከዚህ ቀደም የነበረውን የ3.2% ታክስ ወደ 3.3% እንዲያድግ ባቀረቡት ረቂቅ ላይ ውሳኔ ይሰጣል ተብሏል።
የካውንቲ ኤክስኪውቲቭ የመጀመሪያ እቅድ ከቤት ባለቤቶች ላይ በ3.4% ተመን የሚሰበሰበው ታክስ እስከ3 ቢልየን ዶላር እንደሚደርስና ይህም የካውንቲውን የህዝብ ትምህርት ቤቶች ወጪ እንደሚደግፍ ተናግረው ነበር።

ይሁንና ይህንን እቅዳቸውን ወደጎን አርገው ጠቅላላውን የካውንቲውን ነዋሪ ገቢ በ3.3% በመቅረጥ ያሰቡትን የትምህርት ቤት ድጋፍ ማግኘት እንደሚችሉና በተለይም የመንግስት ሰራተኞች ላይ ጫና እንዳይኖር እንደሚያግዝና ሁሉንም ባማከለ መልኩ እንደሚሰራጭ አስታውቀዋል።
የካውንቲ ኤክስኪውቲቩ አክለውም የካውንቲው ካውንስል አባላት ይህን የታክስ ረቂቅ ካላጸደቁ ከትምህርት ቤቶች ላይ በጀት እንደሚቀንሱና አሁን ካለው የአስተማሪ እጥረት የባሰ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ከካውንቲ ካውንስል አባላት አንዱ የሆኑት አንድሩ ፍሪድሰን በበኩላቸው ይህንን ውሳኔ እንደሚቃወሙና በተለይም ከስራቸው የተፈናቀሉ ሰራተኞችን ድጋሚ ታክስ ማስከፈል ሌላውንም ህዝብ ኑሮው በተወደደበት ወቅት ሌላ ተጨማሪ ወጪ ማድረጉ ፍትሃዊ እንዳልሆነ ተናግረዋል።