
የኢትዮጵያን ኮሚውኒቲ በሜሪላንድ በማስተባበር በሚታወቁት በአቶ አንተነህ ሀብተስላሴ የተጀመረውና እስካሁን ከ730 በላይ ሰዎች በፈረሙበት ፔቲሽን ላይ እንደሚታየው በሞንጎምሪ ካውንቲ ኮሚውኒቲ ኮሌጅ የኢስት ካውንቲ የትምህርት ማዕከል ዳይሬክተር የነበሩትን ዶ/ር ሀምራዊት ተስፋ በድንገትና ያለምንም ማስጠንቀቂያና ምክንያት ከቦታቸው መነሳታቸው አግባብ እንዳልሆነና ይህ ጉዳይ የሚመለከተው የተቋሙ ቦርድ ኦፍ ትረስቲስ ዶ/ር ሀምራዊት በምን አግባብ ከሀላፊነታቸው እንደተነሱ በግልጽ እንዲያሳውቅ ጠይቀዋል።
በዚህ የፊርማ ማሰባሰቢያ ገጽ ላይ እንደተቀመጠው ዶ/ር ሀምራዊት በስራ ዘመናቸው ከ1000 በላይ ተማሪዎች በክሬዲት ፕሮግራም በማስመዝገብ፤ ከ 1500 በላይ ደሞ በ ነን-ክሬዲት በማስመዝገብ የሚታወሱ እንደሆነና በአንድ አመት ውስጥ ብቻ ከ50 በላይ ፕሮግራሞችን ለማህበረሰቡ አዘጋጅተው እንደነበር ተነግሯል።
ዶ/ር ሀምራዊት በስራ ዘመናቸው በፍትሀዊነት ችግር የተጠቁ የጥቁሮችን፤ ስደተኞችን፤ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች እንዲሁም ሌሎችን በማካተት ፕሮግራም ሲያዘጋጁ እንደቆዩና የትምህርት ተቋሙ እነዚህን የማህበረሰብ ክፍሎች ያካተተ እንዲሆን ሲሰሩ ቆይተዋል።
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ወቅት ድረስ የፊርማ ማሰባሰቢያው የ733 ሰዎችን የድጋፍ ፊርማ አሰባስቧል።
የኢትዮጲክ ባልደረቦችም ስለጉዳዩ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ለትምህርት ተቋሙ የቦርድ ኦፍ ትረስቲስ ኤሜይል ልከው እስካሁን ምላሽ አላገኙም።
ዶ/ር ሀምራዊት ከዚህ ቀደም በኢትዮጲክ ተገኝተው ስለ ኮሌጃቸው አገልግሎቶችና እንዲሁም ማህበረሰባችን እንዴት በነኚህ መልካም ዕድሎች መጠቀም እንደሚችል ማስረዳታቸው ይታወሳል።