የፌደራል ይግባኝ ፍርድ ቤት ዲሴምበር 6 በዲስትሪክት ኦፍ ኮሎምቢያ ሰርኪውት በዋለው ችሎት ከዚህ ቀደም ቲክቶክ ለአሜሪካ ባለሀብቶች እንዲሸጥ የተፈረደውን ውሳኔ በማጽናት የቲክቶክ ባለቤት የባይትዳንስን ይግባኝ ውድቅ አደረገ።
በዚህ ውሳኔ መሰረትም ቲክቶክ በዩናይትድ ስቴትስ ባለሀብቶች ካልተገዛ በመጬው ጃንዋሪ አጋማሽ ጀምሮ በዩናይትድ ስቴትስ እንዳይታይ ይታገዳል። የቲክቶክ ባለቤቶች ጉዳያቸውን ይዘው ወደ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይሄዳሉ ተብሏል።
ትላንት ዴሴምበር 13 እንደተሰማው ደሞ በዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስ የቻይና ኮሚውኒስት ፓርቲ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑት ጆን ሙሊናርና ሌላኛው አባል ራጃ ክሪሽናሙርቲ ለአፕልና ለጎግል (አልፋቤት) ሲ.ኢ.ኦዎች በላኩት ደብዳቤ በዲሴምበር 6 በዋሽንግተን ዲሲ የይግባኝ ፍርድ ቤቶች በደረሰበት የፍርድ ውሳኔ ተንተርሶ ቲክቶክን ከአፕስቶርና ከፕሌይስቶር ከጃንዋሪ 19 ጀምሮ እንዲያወርዱ ጠይቀዋል።
በዚህ ደብዳቤ እንደተጠቀሰው በውጭ ጠላቶች ባለቤትነትና ቁጥጥር የሚደረግበትን ማንኛውንም መተግበሪያ (አፕ) በአፕስቶር ወይም በፕሌይ ስቶር ማኖር ህገወጥ እንደሆነ አስገንዝበዋል። አክለውም ለቲክቶክ ባለቤቶች ድርጅቱን በአሜሪካ ለተመዘገበ ተቋም እንዲሸጡ የ233 ቀናት ጊዜ ገደብ እንደሰጧቸውም ጠቁመዋል።
ይህን ተከትሎ የቲክቶክ ባለቤቶች ቲክቶክ ለ1 ወር በአሜሪካ ቢዘጋ የአሜሪካ አነስተኛ የንግድ ተቋማትና ኑሮዋቸውን በቲክቶክ የሚደጉሙ ሰዎች በጠቅላላው ከ1.3 ቢልየን ዶላር በላይ ያጣሉ ብሏል።
እስካሁን መጪው ፕሬዘደንት ትራምፕ ይህንን እርምጃ ይደግፋሉ አይደግፉም የሚለው በውል አልታወቀም።