የአስራ አምስት አመት እድሜ የሆነች ታዳጊ ተማሪ በምትማርበት የክርስትያን የግል ትምህርት ቤት በከፈተችው ተኩስ አንድ አስተማሪና ሌላ በአስራዎቹ እድሜ የሚገኝ ተማሪ ለህልፈት ተዳርገዋል ሲል የማዲሰን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ ፖሊስ ተኳሿን እንደገደላትም ተነግሯል፡፡
የማዲሰን ፖሊስ ቺፍ የሆኑት ሾን ባርነስ ስለተኳሿ ማንነትና በቂ የሆነ መረጃ ባያወጡም ከሟቾቹ ሌላ 6 ሰዎችን እንደቆሰሉና ሁለቱ ለህይወታቸው በሚያሰጋ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ተኩሱ የተደረገበት የአበንደንት ላይፍ ክርስትያን ትምህርት ቤት በውስጡ ከኪንደርጋርተን እስከ 12ኛ የሚማሩ 420 ያህል ተማሪዎች አሉት፡፡ ከቆሰሉት 6 ሰዎች ሁለቱ ለህይወታቸው የሚያሰጋ ጉዳት እንደደረሰባቸው ቺፍ ባርነስ አክለው አስታውቀዋል፡፡ መርማሪዎች እንደሚሉት ተኳሿ 9ሚሊሜትር ሽጉጥ እንደተጠቀመች እንደሚያምኑ ለአሶሼትድ ፕሬስ ጠቁመዋል፡፡
የዊስኮንሲን ገቨርነርም ተጨማሪ መረጃውች እስኪለቀቁ ለተማሪዎቹ፤ ለአስተማሪዎቹና ለመላው የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ በጸሎታቸው እንደሚያስቧቸውና ፖሊስና የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በፍጥነት በቦታው በመገኘት ላደረጉት ምላሽ አመስግነዋል፡፡
ፖሊስ እስካሁን ለወንጀሉ ምክንያት ምን እንደሆነ አጣርቶ እንዳልጨረሰና ከተኳሿ ወላጆችጋም እየተነጋገረ እንደሆነ ወላጆችም ለፖሊስ ቀና ትብብር እያረጉ እንደሆነ የፖሊስ አለቃ የሆኑት ቺፍ ባርነስ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚደንት ባይደንም ይህንን አሳዛኝ አደጋ በመጥቀስ ኮንግረስ በጦር መሳሪያ ግዢ ላይ ቁጥጥር እንዲደረግና የሰዎችን የጦር መሳሪያ ግዢ ከመፈጸማቸው በፊት ማንነታቸውና ከዚህ በፊት የነበራቸውን ሬከርድ ከግምት በማስገባት እንዲሆን እንዲሁም በብሄራዊ ደረጃ የማስጠንቀቂያ ህግ እንዲያወጣ ጠይቀዋል፡፡
ዜናውን ያገኘነው ከWTOP ነው፡፡