ትላንት ጃንዋሪ 1 2025 ንጋት ላይ በኒው ኦርሊንስ የደረሰውን የአሸባሪ ጥቃት ተከትሎ የዲሲ ፖሊስ ሳምንቱን በሙሉ ከፍተኛ ጥበቃ እንደሚያደርግ የፖሊስ ቺፍ ፓሜላ ስሚዝ አስታውቀዋል። የአሜሪካ ዋና ከተማ የሆነችው ዲሲ ከሰሞኑ ሁለት እጅግ ታላላቅ ሁነቶችን ታስተናግዳለች። በመጪው ሳምንት ጃንዋሪ 9 የቀድሞ ፕሬዘደንት የጂሚ ካርተር የቀብር ስነስርዓት የሚፈጸም ሲሆን በጃንዋሪ 20 ደሞ የፕሬዘደንት ትራምፕ ስርዓተ ሹመት ይከናወናል።
ኤፍ ቢ አ ይ የኒው ኦርሊንሱን የሽብር ተግባር የፈጸመው የቴክሳስ ተወላጅ የሆነው የ42 አመቱ አሜሪካዊና የቀድሞው የአሜሪካ መከላከያ ሰራተኛ የነበረው ሸምሰዲን ጀባር እንደሆነና ይህ ግለሰብ ብቻውን ሳይሆን ከሌሎች ግብረ አበሮችጋ ሆኖ ይህን የወንጀል ተግባር እንደፈጸመና ፖሊስ ግብረ አበሮቹን በመፈለግ ላይ እንደሆነ በመግለጫው ጠቁሟል። ሆኖም ጃንዋሪ 2 ፖሊስ ባወጣው መግለጫው ወንጀኛው ብቻውን ይህን የሽብር ተግባር እንደፈፀመና ምንም አጋዥ እንዳልነበረው ተናግረዋል::
የፌደራል ፖሊስ ሸምሰዲን በቦታው እንደተገደለና በመኪናው ውስጥ የአይሲስ ባንዲራ እንደተገኘ አክሎ ገልጿል። በዚህ ጥቃት እስካሁን 15 ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል።
ከሰዓታት በኋላ ሌላ ፍንዳታ በላስቬጋስ የትራምፕ ህንጻ አቅራቢያ ተከስቷል። በቴስላ ስይበር ትራክ ውስጥ የነበር ፈንጂ ፈንድቶ የመኪናውን አሽከርካሪ ሲገድል 10 ያህል ሰዎችን አቁስሏል።
ባለስልጣናት እንዳሉት በላስ ቬጋስ የደረውን ፍንዳታ ያቀናበረ በአሜሪካ መከላከያ የኦፐሬሽን ዳይሬክተርነት እያገለገለ የሚገኘው ማቲው ሊቭስበርገር እንደሆነ አሳውቀዋል::
ከሰሞኑ ታዲያ በኒው ኦርሊንስና በላስ ቬጋስ የደረሱትን አደጋዎች ከግምት በማስገባት የተጠናከረ ጥበቃ በዋና ከተማዋ እንደሚኖር ተነግሯል። ይህን ስጋት ከግምት በማስገባትም የዲሲ ፖሊስ ትላንት በነበረ የዋሽንግተን ዊዛርድ የባስኬትቦል ግጥሚያ የካፒታል ዋን አሪና ለመኪና ተዘግቶ ነበር። ቻይና ታውን የሜትሮ ጣቢያ ላይም ከወትሮ በርከት ያሉ ፖሊሶች እንደነበሩ ተጠቁሟል።
የዲሲ ፖሊስ ባወጣው ኦፊሴላዊ መግለጫ እስካሁን ይህ ነው የሚባል የተረጋገጠ ስጋት ባይኖርም ለጥንቃቄ ሲል ግን ቁጥጥሩን እንደሚያጠብቅና ከፌደራልና ሌሎች ባለድርሻ አካላትጋ በመተባበር ነዋሪዎችንና እንድግዶችን ደህንነት እንደሚያስጠብቅ ተናግረዋል።
ስለ ሸምሰዲን ጃባር ማንኛውም መረጃ ያለው ሰው በስልክ 1-800- CALL FBI በመደወል ወይንም በድረ-ገጻቸው www.fbi.gov/bourbonstreetattack በመሄዽ ጥቆማ መስጠት እንደሚችሉ ፖሊስ አክሎ ገልጿል።