
ፕሬዘደንት ትራምፕ ከተመረጡ በኋላ ከወሰዷቸው እርምጃዎች አንዱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት/AI/ ላይ ግዙፍ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ አቅደዋል። ምንም እንኳ የሰውሰራሽ አስተውሎት ጥቅም እና ጉዳት እያከራከረ ቢሆንም በሀገረ-አሜሪካ የሰውሰራሽ አስተውሎት መሠረተ ልማትን ለመገንባት የ500 ቢሊዮን ዶላር በጀት መድበዋል ። መርሃ ግብሩ «ስታርትጌት» ይባላል። በዚህ ፕሮጀክትም ሶስት ትልልቅ ተቋማት ይጣመራሉ። የቻትጂፒቲ ጠንሳሽ ኦፕን ኤ.አይ.; ሶፍት ባንክና ኦራክል ኮርፖሬሽን ይህንን ፕሮጀክት ለመምራት ከፕሬዘደንት ትራምፕ ፍቃድ ተሰቷቸዋል።
ፕሬዘደንት ትራምፕ ይህን ባወጁበት ወቅት አሜሪካ የሰው ሰራሽ አስተውሎት/AI/ ዋና መናኸሪያ እንደምትሆንና በአለም ላይም በዘርፉ ቀዳሚ እንደምትሆን ተናግረው ነበር።
ይህ ከሆነ ከቀናት በኋላ ታዲያ የቻይናው ጀማሪ የንግድ ተቋም የሆነው ዲፕሲክ የተባለ የሰው ሰራሽ አስተውሎት/AI/ እንደፈበረከና እስካሁን ለህዝብ ከቀረቡት የሰው ሰራሽ አስተውሎት/AI/ መተግበሪያዎች ሁሉ የላቀ እንደሆነ ተናግረው ነበር። ይህንን መተግበሪያ ለመስራትም ከ10 ሚልየን ያነሰ ወጪ እንዳስወጣቸው ጠቁመዋል።
ይህን ተከትሎም ይህ የሰው ሰራሽ አስተውሎት/AI/ መተግበሪያ በአሜሪካ ቀዳሚው ዳውንሎድ የሚደረግ መተግበሪያ ሆኗል። የዲፕሲክ ባለቤቶች ታዲያ የዚህን መተግበሪያ ኮድ ለአለም በሙሉ ክፍት ያደረጉት ሲሆን ይህም የአሜሪካንን የሰው ሰራሽ አስተውሎት/AI/ የበላይነት ህልም መና ሊያስቀረው እንደሚችል በርካቶች ይተነትናሉ።
የዚህን ዜና ተከትሎም በሰው ሰራሽ አስተውሎት/AI/ ላይ አተኩረው የሚሰሩ እንደ ኦራክልና ንቪዳ ያሉ የቴክኖሎጂ ስቶክ ማርኬት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ወድቋል።

የዲፕሲክ ባለቤቶች ዛሬ ሰኞ ጃንዋሪ 27 ባወጡት መግለጫ በመተግበሪያቸው ላይ አዲስ ተመዝጋቢዎችን መቀበል እንዳቆሙ ተናግረዋል። ይህ የሆነበት ምክንያት ደሞ ከፍተኛ የሆነ የሳይበር ጥቃት ስለደረሰባቸው እንደሆነ ተናግረዋል::
መረጃውን ያገኘነው ከሬውተርስ ነው።