ከቨር-1-1

በዩናይትድ ስቴትስ የዲሲ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ ዛሬ እንዳሳወቀው ኦገስት 18 2019 ረፋድ ላይ በ708 Kennedy Street ባለ መኖሪያ ቤት ቤዝመንት ውስጥ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ ወቅት በተጠቀሰው ቤት በቤዝመንት ተከራይተው ይኖሩ የነበሩት የ40 አመቱ ፍጹም ከበደና የ10 አመት ታዳጊው ያፌት ሰለሞን ከአደጋው ለመዳን ከቤት ውስጥ መውጣት ባለመቻላቸው በአደጋው ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡

የክስ መዝገቡ እንደሚያሳየውም የዲሲ እሳት ተከላካዮች በሁለት መቀርቀሪያ የተዘጋውን የቤዝመንት ብረት በር ሰብረው ለመግባት 15 ደቂቃ ፈጅቶባቸዋል፡፡ በሩን ገንጥለው ሲገቡም ታዳጊ ያፌት በሰለሞን እቅፍ ውስጥ እንዳለ ያገኙታል፡፡ ትከሻቸው በሩን ለመክፈል ባደረጉት ሙከራ በልዞ እንደነበርም የሀኪም ሪፖርት ያሳያል፡፡ እሳቱ በተነሳበት ቀን ያፌት የ10 አመት ልደቱን እንዳከበረና ከ2 ቀን በኋላ ለህልፈት እንደተዳረገም ተነግሯል፡፡ 

የያፌት እናት በጆርጅ ዋሽንግተን ሆስፒታል የጽዳት ክፍል እንደምጸራና ያን ዕለትም ወደስራ በለሊት 5፡30 ላይ እንደወጣች ለፍርድ ቤት ተናግራለች፡፡ ልጇ ያፌትም ሁሌ ሲነቃ እንደሚደውልላት ያን ቀን ግን እንዳልደወለላት ይልቅስ የቤት አከራዩዋ ደውሎ  የእሳት አደጋ እንደደረሳና ልጇ ችልድረንስ ሆስፒታል እንደገባ እንደነገራት  ለፍርድ ቤቱ ተናግራለች::

የያፌት አስከሬን መሸኛ ፕሮግራም

ፍጹም ደሞ እዛው ቤዝመንት ሌላ አነስተኛ ክፍል ተከራይቶ ይኖር እንደነበርና  ከኢትዮጵያ ዋሽንግተን ዲሲ ከመጣ በኋላ የአእምሮ መታወክ እንደገጠመውና የቤተክርስትያን ሰዎች ድጋፍ ሲያደርጉለት እንደነበረ በቤተክርስትያን የሚያቁት ሰዎች በፍርድ ቤት ተገኝተው መስክረዋል፡፡ በተጨማሪም እህቱ ከህንድ ኒው ዴልሂ የአርክቴክቸር ዲግሪ እንዳለውና ከሚስቱጋ ወደአሜሪካ እንደመጡ ብዙም ሳይቆዩ እንደተፋቱ መስክራለች፡፡ 

የዲሲ መንግስት ታዲያ የቤት አከራዩን ለአደጋው ተጠያቂ ነው ሲል የከሰሰው ሲሆን በክስ መዝገቡ ላይ እንደሚታየውም አከራይ አደጋው ከመድረሱ በፊት ማርች 21 2019 ላይ ከዲሲ ፖሊስ በርካታ የቤት ህግ ጥሰቶች አሉበት በሚል ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ደርሶት ይነበረ መሆኑንና የዲሲ የማከራይት ፍቃድም እንደሌለው አሳውቀዋል፡፡ 

አከራይ ቤቱን በህገወጥ ሸንሽኖ ሲያከራይ እንደነበረ፤ አንዳንዶቹ ክፍሎች ፈጽሞ መስኮት እንደሌላቸው እንዲሁም የእሳት አደጋ መከላከያ ጭስ አነፍናፊ በቤዝመንት ጨምሮ በክፍሎቹ ውስጥ እንደሌለና ይህም ህገወጥ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ 

ይህን ተከትሎም የቤቱ አከራይ የሆኑት የ 67 አመት አዛውንት ጄምስ ጂ ወከር ዛሬ ፌብሯሪ 20 2025 በዋለው የከፍተኛው ፍርድ ቤት ችሎት ወንጀለኛ ተብለዋል፡፡ 

አደጋው በደረሰበት ወቅትም ፖሊስ 22 የማስጠንቀቂያ እሜይል ለዲሲ ሸማቾች ጉዳይ ቢሮ (DC Department of Consumer and Regulatory Affairs (DCRA)) እንደላከ አስታውቆ ነበር፡፡ የዲሲ DCRA ተወካይም ቤቱን ለማየት የሄደ ቢሆንም ወደቤት ገብቶ አስፈላጊውን ምርመራ ሳያደርግ እንደሄደ የWUSA9 ዘገባ ያሳያል፡፡ በወቅቱ WUSA9 ኢንተርቪው ያደረጋቸውና ከአደጋው በህይወት ከተረፉ 5 ሰዎች አንዷ የሆኑት ዘውድነሽ በናቴ በተደጋጋሚ እንዳመለከቱና በቤቱ ውስጥ በርካታ የኤሌክትሪክ ገመዶች እንደነበሩ ተናግረው ነበር፡፡ 

በወቅቱ ይህ የእሳት አደጋ የዲሲ 911 የድንገተኛ አደጋ የስልክ አገልግሎትን ግድፈትና እክሎች የታየበት እንደሆነ ዘግበን ነበር፡፡ በወቅቱ በተደረገው ኦዲትም ከሌሎች አደጋዎች በተጨማሪ በመስሪያቤቱ ሰራተኞች ግድፈትና ቸልተኝነት ከጠፉት ህይወቶች በኦገስት 18፣ 2019 ኬኔዲ ስትሪት ላይ ተከስቶ የነበረውን የእሳት አደጋ ተከትሎ ለህልፈት የተዳረጉት የ10 አመቱን ያፌት ሰለሞንና የ40 አመቱን ፍፁም ከበደን ተጠቃሽ እንደነበሩ ተጠቁሟል፡፡

About Author

ይህን መረጃ ለወዳጅ ዘመዶችዎ ሼር ያርጉት

Sign In

Register

Reset Password

Please enter your username or email address, you will receive a link to create a new password via email.