ጃንዋሪ 3 2025፡ ሪችመንድ ቨርጂንያ
የቨርጂንያ ገቨርነር ግሌን ያንኪን ዛሬ ጃንዋሪ 3 ማምሻውን ባወጡት መግለጫ በመጪው እሁድ ጀምሮ ይኖራል ተብሎ በተተነበየው የበረዶ ውሽንፍርና ከባድ ስቶርም ምክንያት በግዛታቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥተዋል። በግዛታቸው ያሉ ነዋሪዎች፤ ጎብኚዎችና ቨርጂንያን አቋርጠው ለሚያልፉ ተጓዦች ጥንቃቄ እንዲያደርጉና አስቀድመው እንዲዘጋጁ መክረዋል። እንደ ገቨርነር ያንኪን እሁድ ለመጓዝ ያሰቡ ሰዎች ለጥንቃቄ ሲባል ቅዳሚ ቢጓዙ የተሻለ እንደሚሆንም አክለው ጠቅሰዋል። እሁድ መጓዝ ግዴታ የሆነባቸው ሰዎች ደሞ በመንገድ ላዩ ምልክቶችን እንዲያስተውሉ፤ የሚወጡ ማስጠንቀቂያዎች እንዲተገብሩና ለራሳቸውም ለሌሎችም ደህንነት በማሰብ እንዲንቀሳቀሱ መክረዋል።
የአየር ሁኔታ ትንበያዎች እንደሚያሳዩት ከእሁድ ጀምሮ እስከ ሰኞ ድረስ ከባድ የበረዶ ውሽንፍርና የበረዶ ዝናብ ሊኖር እንደሚችልና ይህንን መጥፎ የአየር ሁኔታ ተከትሎ ከባድ ውርጭና ቅዝቃዜ እንደሚመጣ ይህም ለህይወት ሁሉ አስጊ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። የቨርጂንያ መንግስት ትራንስፖርት ቢሮ ይህን ከግምት በማስገባት አሽከርካሪዎችና እግረኞች እንዳይቸገሩ መንገዶቹ ላይ ጨው የመነስነሱን ስራ ከዛሬ አርብ ጃንዋሪ 3 ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረግ እንደሆነ ተነግሯል። በተለይም አስቀድመው የሚቀዘቅዙ ድልድዮችን በአግባቡ በጨው የማከም ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ተብሏል።
የቨርጂንያ ስቴት ፖሊስ ደሞ እሁድና ሰኞ ከወትሮው በተለየ በርካታ የፖሊስ ጉዶቻቸውን እንደሚያሰማሩና ለህዝቡ አስፈላጊውን የድጋፍ አገልግሎት ለመስጠት እንደተዘጋጁ ተናግረዋል።
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የሚኖርን አላስፈላጊ የትራፊክ መጨናነቅ ለማስቀረትም ሰዎች የግድ ካልሆነባቸው መኪና ባያሽከረክሩ እንደሚመረጥ ተናግረዋል። የግድ ከሆነና ማሽከርከር ካለባቸው ደሞ የሚከተሉትን ምክሮች ተግባራዊ እንዲያደርጉ መክረዋል።
- የፊት መብራት መጠቀም – አሽከርካሪዎች መብራታቸውን በማብራት ከሌላ ወገን በሚመጣ አሽከርካሪም ሆነ እግረኛ የመታየት እድላቸው ከፍ ይላል።
- ፍጥነትን ቀንሶ ማሽከርከር – በንዲህ ያለ አስቸጋሪ ወቅት ፍጥነትን ቀንሶ ማሽከርከር ሊከሰቱ ከሚችሉ አደጋዎች ይታደጋል። መሬቱ ቢያንሸራትት ወይንም መቆም ቢያስፈልግዎ አነስተኛ ፍጥነት ላይ ከሆኑ በቀላሉ መኪናዎን ማቆም ይችላሉ።
- ሌሎች መኪኖችን ተጠግተው አያሽከርክሩ – አንዳንዴ በረዶ ላይ እየነዱ ለመቆም ፍሬን ሲይዙ መኪናዎ ሊንሸራተት ስለሚችን ያንን ከግምት አስገብተው ያሽከርክሩ።
- የደህንነት ቀበቶዎን ይታጠቁ – በአብዛኛው በበረዶ ጊዜ የሚደርሱ አደጋዎች የሚከሰቱት መኪኖች ከመንገድ ዳር ካሉ የመከላከያ ብረትጋ ሲጋጩ ነው። በእንዲህ ያለ ወቅት የደህንነት ቀበቶዎን ወይም ሲት ቤልት ካላረጉ መኪናዎ ሲጋጭ እርስዎ መኪናው ውስጥ ይላተሙና ለከባድ ጉዳት ይዳረጋሉ።
- ከቤትዎ አይውጡ – ግዴታ ካልሆነ ከቤትዎ አይውጡ።
በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ከተቀመጡት መመሪያዎች አንዱ በ7ኛ ተራ ቁጥር የተቀመጠውና በመጪው ማክሰኞ ጃንዋሪ 7 2025፤ በቨርጂንያ የሚደረገውን የፕራይመሪ ምርጫ በዚህ የአየር ሁኔታ እንዳይስተጓጎል የቨርጂንያ ምርጫ ኮሚሽን በህግ የተፈቀደለትን ሀይል አሟጦ በመጠቀም በዲስትሪክት 26 ለኮንግረስ እንዲሁም በዲስትሪክት 10ና 32 ለሴኔት የሚደረጉ ልዩ ምርጫዎች ላይ ህጋዊ መራጮች እንዲሳተፉ አስፈላጊውን ሁኔታ እንዲያመቻቹ አመራር ተሰቷል።
ይህንን በማስመልከትም ገቨርነር ያንኪን መራጮች ነገ ቅዳሜ ጃንዋሪ 4 ውሽንፍሩ ሳይጀምር ወደ ምርጫ ጣቢያዎቻቸው በመሄድ ድምጻቸውን እንዲሰጡ መክረዋል።
በተጨማሪም የቨርጂንያ ናሽናል ጋርድ በተጠንቀቅ እንዲጠብቅ ተደርጓል። ሙሉውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማየት ይህን ሊንክ ተከትለው ይሂዱ።