
በሬገን ኤርፖርት አቅራቢያ አውሮፕላንና ሄሊኮፕተር ተጋጭተው ፖቶማክ ወንዝ ላይ እንደወደቁ በርካታ ባለስልጣናት አስታወቁ።
ማምሻውን የፌደራል አቪዬሽን ባለስልጣንን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በፒ ኤስ ኤ አየርማንገድ የሚተዳደር ቦምባርዲየር CRJ700 ጄት በረገን አየርማረፊያ መንደርደሪያ 33 ላይ ለማረፍ በሚዘጋጅበት ወቅት ከSikorsky H-60 ወይም በተለምዶ ብላክ ኃውክ ከተባለ የሚሊተሪ ሄሊኮፕተርጋ በአየር ላይ በመጋጨቱ አደጋው ሊደርስ ችሏል።
እንደ መከላከያ ባለስልጣናት ከሆነ በሄሊኮፕተሩ ውስጥ 3 ወታደሮች ነበሩ።
አውሮፕላኑ 60 ተሳፋሪዎችና 4 ሰራተኞች ይዞ እንደነበርም ተነግሯል። የፒ ኤስ ኤ አየርመንገድ አውሮፕላኑን ለአሜሪካን ኤርላይንስ ያበረው እንደነበር እና የአሜሪካን ኤርላይንስም ተጨማሪ መረጃዎች እንድደረሱት ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አሳውቋል።
ይህንን አደጋ ተከትሉ ማንኛውም የአውሮፕላን ትራፊክ በሬገን አየር ማረፊያ እንዲቆም ታዟል።
የዲሲ ፖሊስን ጨምሮ በርካታ የአደጋ ተከላካይ ሰራተኞች በነፍስ ማዳን ስራ ተጠምደዋል። የፌርፋክስ ካውንቲ የነፍስ አድን ሰራተኞች ጀልባዎቻቸውን ወደ ፖቶማክ ወንዝ በማስገባት የተረፉ ሰዎችን የማዳን ስራውን ተቀላቅለዋል።
የዲሲ ሜትሮም በረራቸው የተስተጓጎለባቸውንና ወደ ደለስ ኤርፖርት የተላኩ ተጓዦች እንዳይጉላሉ ተጨማሪ የሲልቨር ላይን ባቡሮች እንደሚያሰማሩ አስታውቀዋል።
ፕሬዘደንት ትራምፕም በደረሰው አደጋ እንዳዘኑና ለተጎጂዎች ምህረትን ለነፍስ አድን ሰራተኞች ብርታትን ተመኝተው ጉዳዩን በአንክሮ እየተከተታተሉ እንደሆነና ተጨማሪ መረጃ እንደደረሳቸው እንደሚያጋሩ በቃል አቀባያቸው በኩል አሳውቀዋል።

አሜሪካን ኤርላየንስ ማምሻውን እንዳሳወቀው በዚህ በረራ ላይ ወዳጅ ዘመድ ያላቸው ሰዎች በስልክ ቁጥር 880-679-8215 እንዲደውሉ መክሯል::
