
Image Credit: MCPS
ባሳለፍነው ጃንዋሪ 29 2025 የሞንጎምሪ ካውንቲ የህዝብ ትምህርት ቤቶች እንዳስታወቀው ማህሌት አየለንና ኤፍራታ ጥበቡን ጨምሮ 13 ተማሪዎች ከኩዌስት ብሪጅ ባለሙሉ ስኮላርሺፕ ባለቤት እንደሆኑ አስታውቋል።
ኩዌስት ብሪጅ አገር አቀፍ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሲሆን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች የተገኙ በጣም ጎበዝ ተማሪዎችን ሙሉ ስኮላርሺፕ ድጋፍ በማድረግ ከ50 በላይ ከሚሆኑ ኮሌጆችና ዩኒቨርስርቲዎችጋ እንዲገናኙ ያደርጋል።
ማህሌት አየለ ስለዚህ መልካም አጋጣሚ ስትናገርም “ወላጆቼ ወደዚህ አገር የመጡበት ዋነኛ ምክንያት እኔና እህቴ የተሻለ የትምህርት እድል እንድናገኝ እንደሆነ አውቃለሁ” ብላለች። ማህሌትና ቤተሰቦቿ በልጅነቷ ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ እንደመጡም በመግለጫው ላይ ተነግሯል።
ማህሌት አክላም ‘“የመጀመሪያ ትውልድ ስደተኛ ቤተሰብ እንደመሆኔ የኩዌስትብሪጅ ስኮላርሺፕ ለኔ ትልቅ ነገር ነው” ካለች በኋላ “ስኮላርሺፑን በማግኘቴ ቤተሰቦቼን እንዳኮራሁ ይሰማኛል አልፎ ተርፎም እዚህ አገር የመጡበትን አላማ እንዲሳካ እንዳደረኩም ይሰማኛል። ይህ ስኮላርሺፕ ትምህርቴን በጥሩ ዩኒቨርስቲ እንድጨርስ ያደርገኛል ለዚህም በጣም አመሰግናለሁ” ብላለች። ማህሌት በቀጣይ በታዋቂው የኖርዝዌስተርን ዩኒቨርስቲ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቷን የምትከታተል ይሆናል።
በጠቅላላው ከሞንጎምሪ ካውንቲ 13 ሲንየር ተማሪዎች ለዚህ መልካም እድል የተመረጡ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ናኦል ደምሴ ከሪቻርድ ሞንጎምሪ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ቺካጎ፤ ሊያ ነጋሽ ከሞንጎምሪ ብሌይር ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደ ማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (MIT)፤ እንዲሁም ኤፍራታ ጥበቡ ከስፕሪንግብሩክ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደ ዴኒሰን ዩኒቨርስቲ እንደሚሄዱ በመግለጫው ተዘግቧል።