
በዲሲ ከንቲባ ስም የተሰየመውና የባውዘር ህግ (Bringing Oversight to Washington and Safety to Every Resident” (BOWSER) Act) ተብሎ የተሰየመው ረቂቅ ህግ ባሳለፍነው ሳምንት ሐሙስ ፌብሯሪ 6 2025 በዩታህ የሪፐብሊካን ሴናተር ማይክ ሊ እና በቴኒሲ ሪፐብሊካን ተወካይ አንዲ ኦግልስ በሁለቱም የመወሰኛ ምክር ቤቶች (ሴኔትና ኮንግረስ) ለውይይት ቀርቧል፡፡
ይህ ህግ በዋናነት በ1973 ተረቅቆ የጸደቀውን (District of Columbia Home Rule Act of 1973) የዲሲ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሽሮና አሁን ያለውን አስተዳደራዊ መዋቅር በትኖ የከተማዋ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ በኮንግረስ ስር እንዲውል እንዲሆን ይጠይቃል፡፡
በ1973ቱ የራስን በራስ የማስተዳደር ህግ መሰረት የዲሲ ነዋሪዎች ከንቲባቸውንና የየዋርዱን የካውንስል አባላት እንዲሁም ሌሎች መሪዎችና አስተዳዳሪዎች እንዲመርጡ የሚፈቅድ ሲሆን የአሜሪካ መወሰኛ ምክርቤቶች ወይንም ኮንግረስ በበላይነት የቀረቡለትን ህጎች የመመርመርና የማሳለፍ ስልጣን ብቻ ነበረው፡፡

አዲሱን የዲሲን አስተዳደራዊ መዋቅር በኮንግረስ እንዲካተት የጠየቁ የምክር ቤት አባላት በዋናነት ለዚህ እንደምክንያት የሚያቀርቡት በከተማዋ የተንሰራፋውን ህገወጥነት፤ የወንጀል መስፋፋት፤ የሙስና መስፋፋት፤ እንዲሁም የአሜሪካ ዜግነት የሌላቸው ሰዎች በምርጫ እንዲሳተፉ የዲሲ መንግስት መፍቀዱን በመቃወም የከተማዋን የራስን በራስ ማስተዳደር ህግ እንዲሻር ጠይቀዋል፡፡
የዋርድ 8 ካውንስል አባል የሆኑት የትሬዮን ዋይት የሙስና ውንጀላና የፌደራል ወንጀል ክስን እንዲሁም በከተማዋ የሚስተዋለውን በጦር መሳሪያ የታገዘ የመኪና ዝርፊያ እንደምሳሌ በረቂቁ ላይ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በህዝብ ትራንስፖርት ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ የተደበደቡ ሰዎች፤ በኮንግረስ አባላትና በደጋፊ ሰራተኞቻቸው ላይ የደረሱ ዝርፊያዎችን እንደ ምክንያት አቅርበዋል፡፡
ይህ ህግ ሆኖ እንዲጸድቅ ከተወሰነ ዋሽንግተን ዲሲ ለ50 ዓመታት የተዳደረችበት የራስን በራስ የማስተዳደር ህግ (District of Columbia Home Rule Act of 1973) ከአንድ አመት በኋላ ተሽሮ ከተማዋ ሙሉ ለሙሉ በኮንግረስ አስተዳደር ስር ትውላለች፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎችም እንደቀድሞው ከንቲባቸውንና የካውንስል አባሎቻቸውን መምረጥ አይችሉም፤ ይልቅስ ኮንግረስ የከተማዋን አስተዳዳሪና በየዘርፉ ያሉ ባለሟሎችን በሹመት ይሰይማል፡፡
ይህ ህግ ከመጽደቁ በፊት በርካታ ተግዳሮቶችና ተቃውሞች እንደሚጠብቁት ይታመናል፡፡