
በቨርጂንያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ
የቨርጂንያ ገቨርነር ግሌን ያንኪን ዛሬ ፌብሯሪ 10 ባወጡት መግለጫ ከነገ ጀምሮ ይኖራል ተብሎ በተተነበየው የበረዶ ውሽንፍርና እስከ 8 ኢንች የሚገመት የበረዶ ክምችት ትንበያ ምክንያት በግዛታቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥተዋል። በግዛታቸው ያሉ ነዋሪዎች፤ ጎብኚዎችና ቨርጂንያን አቋርጠው ለሚያልፉ ተጓዦች ጥንቃቄ እንዲያደርጉና አስቀድመው እንዲዘጋጁ መክረዋል።
እንደ ገቨርነር ያንኪን ከሰኞ ምሽት ጀምሮ ሁሉም ቨርጂንያውያን የአየሩን ሁኔታ እንዲከታተሉ አስገንዝበዋል። በዚህ ወቅት መጓዝ ግዴታ የሆነባቸው ሰዎች በመንገድ ላዩ ምልክቶችን እንዲያስተውሉ፤ የሚወጡ ማስጠንቀቂያዎች እንዲተገብሩና ለራሳቸውም ለሌሎችም ደህንነት በማሰብ እንዲንቀሳቀሱ መክረዋል።
የአየር ሁኔታ ትንበያዎች እንደሚያሳዩት ከማክሰኞ ጀምሮ እስከ ረቡዕ ድረስ ከባድ የበረዶ ውሽንፍርና የበረዶ ዝናብ ሊኖር እንደሚችልና ይህንን መጥፎ የአየር ሁኔታ ተከትሎ መጏጏዝ አዳጋች እንደሚሆን ተነግሯል::
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የሚኖርን አላስፈላጊ የትራፊክ መጨናነቅ ለማስቀረትም ሰዎች የግድ ካልሆነባቸው መኪና ባያሽከረክሩ እንደሚመረጥ ተናግረዋል። የግድ ከሆነና ማሽከርከር ካለባቸው ደሞ የሚከተሉትን ምክሮች ተግባራዊ እንዲያደርጉ መክረዋል።
- የፊት መብራት መጠቀም – አሽከርካሪዎች መብራታቸውን በማብራት ከሌላ ወገን በሚመጣ አሽከርካሪም ሆነ እግረኛ የመታየት እድላቸው ከፍ ይላል።
- ፍጥነትን ቀንሶ ማሽከርከር – በንዲህ ያለ አስቸጋሪ ወቅት ፍጥነትን ቀንሶ ማሽከርከር ሊከሰቱ ከሚችሉ አደጋዎች ይታደጋል። መሬቱ ቢያንሸራትት ወይንም መቆም ቢያስፈልግዎ አነስተኛ ፍጥነት ላይ ከሆኑ በቀላሉ መኪናዎን ማቆም ይችላሉ።
- ሌሎች መኪኖችን ተጠግተው አያሽከርክሩ – አንዳንዴ በረዶ ላይ እየነዱ ለመቆም ፍሬን ሲይዙ መኪናዎ ሊንሸራተት ስለሚችን ያንን ከግምት አስገብተው ያሽከርክሩ።
- የደህንነት ቀበቶዎን ይታጠቁ – በአብዛኛው በበረዶ ጊዜ የሚደርሱ አደጋዎች የሚከሰቱት መኪኖች ከመንገድ ዳር ካሉ የመከላከያ ብረትጋ ሲጋጩ ነው። በእንዲህ ያለ ወቅት የደህንነት ቀበቶዎን ወይም ሲት ቤልት ካላረጉ መኪናዎ ሲጋጭ እርስዎ መኪናው ውስጥ ይላተሙና ለከባድ ጉዳት ይዳረጋሉ።
- ከቤትዎ አይውጡ – ግዴታ ካልሆነ ከቤትዎ አይውጡ።
ሙሉውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማየት ይህን ሊንክ ተከትለው ይሂዱ።