
በቨርጂኛ የላውደን ካውንቲ ፖሊስ ሰኞ ፌብሯሪ 24 2025 እንዳስታወቀው በግምት ወደ 1 ነጥብ አራት ሚልየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ከአጭበርባሪዎች መያዙን አስታውቋል፡፡ ይህ በተለምዶ የአሳማ ዕርድ (Pig Butchering) የተባለ የማታለያ መንገድን በመጠቀም ሰዎችን የለፉበትን ገንዘብ በማታለል የሚወስዱበት ስልት እንደሆነና በርካቶች በዚህ ስልት በመታለል ገንዘባቸውን አሳልፈው እንደሚሰጡ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ከተበዳዮች አንዱ በተሳሳተ የቴክስት ሜሴጅ በጀመሩት ንግግር ወደ ክሪፕቶ ንግድ እንደገቡና በተለያየ ጊዜ አነስተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወደ መነገጃው ድረ ገጽ እንዳስገቡ በኋላ ላይ ገንዘባቸውን ለማውጣት ሲሞክሩ ለመጀመሪያው ዙር በአነስተኛ ገንዘ እንደሞከሩና እንደተሳካላቸው ኋላ ላይ ግን ዳጎስ ያለ ገንዘብ ለማውጣት ሲሞክሩ ታክስ ይደረጋሉ እንደተባሉና ገንዘባቸው በዛው እንደቀለጠ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጲክ አንባቢዎችም በተለያየ ጊዜ የተለያዩ መረጃዎችን ያደረሱን ሲሆን በወቅቱም መረጃዎቹን ማጋራታችን ይታወሳል፡፡

ከአንባቢዎቻችን አንዱ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን የዚህ ወንጀል ሰለባ እንደሆኑና በተለይም ኢትዮጵያውያን ራሳቸው በዚህ ወንጀል ላይ እንደሚሳተፉና ማንኛውም ሰው ከገንዘብጋ የተያያዘ በጣም የሚያጓጓና ቶሎ ትራፋማ የሚያደርግ መረጃ ይዞ ሲመጣ ሰዎች እንዲጠራጠሩና እንዲጠነቀቁ መክረዋል፡፡

ፖሊስም ለማታውቁት ሰው በፍጹም ገንዘብ አትላኩ፤ ገንዘባችሁን ኢንቨስት የምታደርጉበት ፕላትፎርም ህጋዊ መሆኑን አረጋግጡ ብሏል፡፡ መረጃውን ያጋራንን ነሲቡን እናመሰግናለን፡፡