
ኢትዮጲክ- እንግዳችን ስለሆንሽ እናመሰግናለን።እስቲ በቅድሚያ እራስሽን ለአንባቢዎቻችን አጠር አድርገሽ አስተዋውቂልን።
መቅደስ – አመሰግናለሁ። ስሜ መቅደስ ገ/ወልድ ሆንዱራ ይባላል። ያው በኢትዮጵያ ስሜ መቅደስ ገብረወልድ ነው። እዚህ ሀገር ስመጣ ደግሞ አያቴ ነግሷል። በሙያዬ የአመራር ክህሎት የማማከር አገልግሎት (ማኔጅመር ኮንሰልታንሲ) ባለሞያና አሰልጣኝ ነኝ። በሥራ አለም የ18 ዓመታት ልምድ ያለኝ ሲሆን፤ ላለፉት 11 ዓመታት ደግሞ አሻጋሪ ኮንሰልታንሲ የተሰኘ የራሴን ተቋም መስርቼ እየሰራሁ ነው።
ኢትዮጲክ- አሻጋሪ ኮንሰልታንሲ በዋናነት ምን ላይ ነው የሚሰራው? አሻጋሪስ እንዴት ሊሰኝ ቻለ?
መቅደስ – አሻጋሪ የተወለደው ከህመም ነው። ብዙዎቻችን ከህመማችን ነው የህይወት ዓላማችንን የምናገኘው። እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግስት ተቋም ውስጥ ሰርቼ አውቃለሁ፣ አስተማሪም ነበርኩ፣ የሀገር በቀል እና የአለም አቀፍ ግብረሰናይ ተቋማት ውስጥም ተቀጥሬ ሰርቼ አውቃለሁ። ስለዚህ በነበረኝ የሥራ ዓለም ተሞክሮ ሁሉንም ነካክቼ አልፌዋለሁ። ሁሉም ስፍራ በተመሳሳይ ያየሁት አንድ ነገር ቢኖር የሰዎችን አቅም በአግባቡ መጠቀም የማይችሉ ተቋማትን ነው። ተቋማቱ የገንዘብ አያያዝ ላይ ጎበዝ ናቸው፣ የሪሶርስ ወይም ሀብት አጠቃቀም ላይም ጎበዝ ናቸው እንዲሁም ሌሎች ነገሮች ላይ ጎበዝ ናቸው። ነገር ግን ያላቸውን የሰው ሃይል ሀብት/ሂውማን ሪሶርስ ካፒታላቸው በአግባቡ መጠቀም አይችሉም። ለምሳሌ፦ ባለሞያ የሆነ የፋይናንስ ሰራተኛ ቀጥረው ሲያበቁ ሥራውን በነበረው መልኩ እንዴት አስቀጥሎ እንደሚሰራ ነው የሚነግሩት እንጂ፤ ሰውዬው የሚያመጣውን አዲስ ሃሳብ ተቀብለው ለመሞከር አይፈልጉም። ስለዚህ አብዛኞቹ የማያድጉ ድርጅቶች እንደሚሆኑ ነበር የማየው። ከዛ ነው አሻጋሪ የተወለደው። “ይሄንን ነገር እያጣችሁት ነው…ይህንን ክፍተት ብንሞላው” ብዬ ነው የተነሳሁት። እንዲህ ስናደርግ ደግሞ የተቋማት ባህል የምንለውን ኦርጋናዜይሽናል ካልቸር መለወጥን ያመጣል። በግሌ ከልጅነቴ አንስቶ ግሮውዝ እና ትራንስፎርሜሽን/ እድገት እና ሽግግር ላይ መስራት፣ ያስደስተኛል። እንግዲህ አሻጋሪም የሚያሻግር ከሚለው ጋር ተያይዞ ነው ስሙ የመጣው።
ኢትዮጲክ- ድርጅትሽ ኢትዮጵያ ውስጥ ከብዙ ተቋማት ጋር በትብብር መሥራቱን ድረ ገጻችሁ ያመላክታል። እስቲ ስለኢትዮጵያ ተሞክሮ እና ልምድሽ ትንሽ አጋሪን።
መቅደስ – ኢትዮጵያ ውስጥ ሴት አማካሪ እንዲሁም የመጀመሪያው የድርጅት/ የተቋም ባህል እና ባህሪ የሚያጠና ተቋም መሆኑን ለማስረዳት እና ሥራ አብሮ ከተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት ብዙ ትላልቅ መሰናክሎችን አልፌያለሁ/አልፈናል። እንደውም የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ለተለያዩ ተቋማት ሥልጠና ስንሰጥ የነበረው በነጻ ነው። ሥልጠናውን በነጻ ሰጥተንም አበልም ይጠይቁናል። ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዛ ነው ስልጠና አበል አለው። ከዛ በኋላ ነው ከብዙ ትላልቅ ድርጅቶች እና ፕሮጀክቶች ጋር የመስራት ዕድሉ የመጣው።…ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ የቀድሞ ንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር፣ ከህጻናትና ሴቶች ሚኒስቴር እና ከብዙ መንግስታዊ ተቋማት ጋር አብረን ሰርተናል። በመስተዳድር ደረጃም ከአዲስ አበባ መስተዳድር እና ከኦሮሚያ ጋር እንዲሁም ከስምንት በላይ ዩኒቨርስቲዎች ጋርም ሰርተናል።
ኢትዮጲክ- በወቅቱ ከስልጠናው በኋላ የነበረው ምላሽ ምን ይመስላል? ውጤታማነታችሁስ?
መቅደስ – አዎ…እኛ እንግዲህ የአገልግሎት ኢንደስትሪ ነን። የባህሪ ሽግግር እና ለውጥ ደግሞ በአንዴ የሚመጣ እና የሚታይ ነገር አይደለም። ነገር ግን ደግሞ ስልጠናውን ስንሰጥ ሰዎች ግንዛቤ ሲፈጥሩ እና አሃ ሲሉ እናያለን። ምክንያቱም ከእነዚህ ተቋማት ጋር ዘላቂ የሆነ ትስስር እና ተከታትለን የምንመዝንበት መንገድ የለም። በስልጠናው ወቅት እና በተደጋጋሚ ከሚጋብዙን ተቋማት ግን የምንሰማቸው ምላሾች ግን “ምነው ቀደም ብዬ ይሄንን ነገር ባውቅ ኖሮ ዛሬ የተለየ ቦታ ላይ ነበርኩ” የሚሉ አሉ። እንዲሁም ደግሞ “ይሄንን ሥልጠና አለቆቻችን ቢወስዱት ተቋሙ በጣም ይቀየር ነበር” የሚሉ ግንዛቤ መዳበሩን የሚያመላክቱ በጎ ምላሾን እናገኝ ነበር።
ኢትዮጲክ- የተቋሟት ባህሪን(ኦርጋናይዜሽናል ካልቸር) መቀየር ስንል ምን ማለታችን ነው?
መቅደስ – የተቋም ባህል እና ባህሪ ጥልቅ ነገር ነው። እንደሰው ብንወስደው አንድን ሰው ስናውቀው እና ቀረብ ብለን ስናየው እንዳለው ዓይነት፤ ተቋማትም የራሳቸው የሆነ ባህሪ አላቸው። ሰራተኞች እርስ በርስ ያላቸው ቅርርብ፤ ደንበኛን የሚያስተናግዱበት መንገድ በፈገግታ ነው ወይስ በማመናጨቅ በሚለው ውስጥ የተቋሙ ባህሪ ይታያል። አንድ ሰው ለምሳሌ፦ አሻጋሪ መቀጠር ፈልጎ ስልክ ቢደውል እና እዛ የሚሰራውን ሰው ቢጠይቅ የሚጠይቀው ስለድርጅቱ ራዕይና ተልዕኮ አይደለም። በዋናነት ተቋሙ ውስጥ ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል? ጤና የሚነሳ/ቶክሲክ ነው ወይስ ጤናማ? የሚለውን ነው። “ደግሞስ በሥራው ላይ ማደግ እችላለሁ? የተቋሙ ህግና መመሪያ ምን ይመስላል? የማድግበት ዓይነት ነው ወይ?” የሚለውን ነው። ይሄንን ነው የተቋማት ባህሪ እና ባህል የምንለው። ይሄንን እና ብዙ ነገሮችን ነው የምንሰራው።…
ኢትዮጲክ- እዚህ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ መጥተሽ ተቋም ለመመስረት መነሻ የሆነሽ ያየሽው ክፍተት መንድነው?
መቅደስ – ቴንኪው በጣም…እዚህ ሀገር እንግዲህ ድርጅቱ ከተመሰረት አንድ ዓመት ከአንድ ወር ሆኖታል። ያየሁት ክፍተት ምንድነው? እኔ ሜሪላንድ ነው የምኖረው። እዚ ሲልቨር ስፕሪንግ አካባቢ ደግሞ ብዙ የኢትዮጵያውያን ድርጅቶች አሉ። ቀርብ ብዬ ያነጋገርኳቸውም የንግድ ባለቤቶችም ነበሩ። እና በቃ ስናወራ ያየሁት ነገር ቢኖር፤ በቃ ልክ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደምንሰራው ነው (ንግዳቸውን) እየሰሩ ያሉት። እዚህ ሀገር ብዙ አማራጮች እና ዕድሎች አሉ። የአሜሪካ መንግስት አንስተኛ ንግዶችን እጅግ ያበረታታል።… ሆኖም ብዙዎቹ ከመንግስት የሚመጣውን ድጋፍ አያዩም። ልክ እንደኢትዮጵያ ካሽ እጃቸው ላይ እንስኪኖራቸው ጠብቀው ነው ንግድ የሚከፍቱት። አብዛኞቹም ብዙ አማራጭ ቢኖርም ንግዳቸው ሲያድግ አላየሁም። ከመግስት አካላት እና ከምኖርበት ካውንቲ ጋር አብሮ መስራት ይችላል አይቻልም? የሚለውን እኔ በራሴ ድርጅት ነው የሞከርኩት። ከጠበቅኩት በላይ ድጋፍ አግኝቻለሁ። ከዛ በኋላ ነው እንግዲ ማኅበራሰብችንን “የቱ ጋር ናችሁ? ምን ዓይነትስ ድጋፍ ትፈልጋላቹ?” ማለት የጀመርኩት። የንግድ ሃሳብ ኖሯችሁ ቁጭ ያላችሁ ሰዎችም ኑ እንደግ በሚል ነው ድርጅቱ እየሰራ ያለው።….ገና ማኅበረሰቡን እያነቃን ነው። ማርኬቲንግ ላይ ነን። ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር ለምሳሌ ከስፓኒሽ ኮሚኒቲዎችም ጋር እየተገናኘሁ እንዴት እንደሚሰሩ ልምድ እቀስማለሁ። መልካም ነገር ተምሮ መኮረጅ ጥሩ ነው። ሌሎች ኮሚኒቲዎችንም እያየሁ ነው። እዛ ላይ ነው የምንሰራው እንግዲህ።፡
ኢትዮጲክ- በግል ህይወትሽ ደግሞ የልጆች እናትም ነሽ፤ ተቋም እየመሩ ማኅበረሰብን ማስተባበር ልጅችን ማሳደግ ምን ይመስላል?
መቅደስ – ከኢትዮጵያ ጠቅልዬ እዚህ ሀገር ከመጣሁ በጠቅላላው አንድ ዓመት ከስምንት ወር ሆኖኛል። ባለትዳር ነኝ። ልጆችም አሉኝ። እንደውም የመነቃቃቴ/የሞቲቬሽኔ ምንጮች እነሱ ናቸው። እዚህ ሀገር እንግዲህ ሚድል ስኩል እና ሀይስኩል ነጻ ነው።ነገር ግን ደግሞ ኮሌጅ በስኮላርሺፕ ካልሆነ ተከፍሎ እጅግ ከባድ ነው። ስለዚህ አንድም ሥራውን የምሰራው፤ከልጆቼ እኩል ማደግ የሚችል ነገር መሰራት አለበት በሚል ነው። በእርግጥ እዚህ ሀገር ሲመጣ ኢትዮጵያ ከተለመደው ውጭ ስለሆነ የሚያግዝ ሰው ባለመኖሩ ደጅም ጉዷም ሁሉም ጋር ተገብቶ ተሰርቶ ስለሆነ ትንሽ ያንገጫግጫል። እኔም እንደዛ ገጥሞኛል። የቤቱም የደጁም የሚሰራበት የካፒታሊስት ስርዓት ከባድ ነው። ነገር ግን ቁርጠኝነቱ ካለ ሥራ የማንይንቅ ሰው አሜሪካ ውስጥ ተርቦ አያድርም። እዚህ ትልቁ ጥበብ 24 ሰዓቱን አብቃቅቶ እንዴት ውጤታማ መሆን ይቻላል የሚለው ነው። በእርግጥ አንዳንዴ ከማኅበራዊ ህይወት ላይ የሚቀነስ ነገርም አለ።
ኢትዮጲክ- እራሳቸውን ማሳደግ እንዲሁም ከተቋምሽ ጋር አብረው ለመስራት የሚፈልጉ ሰዎች እንዴት ሊያገኙሽ ይችላሉ?
መቅደስ – ቢሯችን ያለው ሲልቨር ስፕሪንግ 8070 ጆሪጂያ አቬኑ ላይ ነው። በዲሲ እና በሲልቨር ስፕሪንግ ድንበር ላይ ነን። በስልክ ለመደወል የሚፈልጉ ሰዎች ደግሞ 240-904-0008 ላይ ሊደውሉልን ይችላሉ። አብረውን የሚሰሩ ካሉም ይምጡ። እንዲሁም ሥራ ለመጀመር የገንዘብ ድጋፍ/ግራንት ለሚፈልጉም የሚያገኙባቸውን አማራጮች እናግዛለን። ተቋም ለመመስረት ለሚፈልጉም የተለያዩ የምስክር ወረቀቶችን እንዲያገኙ እንረዳለን። በተጨማሪም ተቋም ኖሯቸው አመራራቸውን ለመቀየር ለሚሹ የተቋማቸውን ቅርጽ መለወጥ የሚፈልጉ ድርጅቶችንም እናግዛለን።
ኢትዮጲክ- መቅደስ የኢትዮጲክ እንግዳ ስለሆንሽ በእጅጉ እናመሰግናለን
መቅደስ – እኔም ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ