
የቴክሳስ ፖሊስ እንዳሳወቀው ማርች 14 በ3100 N IH 35 SB (between Parmer Ln & Howard Ln). በተከሰተ የመኪና አደጋ 17 መኪኖች ሲጋጩ አንድ ታዳጊና አንድ አራስን ጨምሮ በጠቅላላው 5 ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል። ፖሊስ አደጋውን አድርሷል ያለውን ተጠርጣሪ የ37 አመት እድሜ ያለው ሰለሞን አርአያ እንደሆነና በወቅቱ ፖሊስ በመጠጥ ወይም በአደንዛዥ ዕጽ ተጸዕኖ ውስጥ ሆኖ ሲያሽከረክር እንደነበር ጠቅሶ በ5 ሰክሮ በማሽከርከር የነፍስ ማጥፋት ወንጀሎችና በ2 ሰክሮ በመተንኮስ ወንጀሎች ክስ መስርቶበት ነበር፡፡
ከሳምንታት በኋላም የደም ምርመራው የቶክሲኮሎጂ ውጤት የታወቀ ሲሆን በውጤቱ ሰለሞን በደሙ ውስጥ ምንም አይነት አልኮሆልም ሆነ አደንዛዥ ዕጽ እንዳልተገኘበት ተረጋግጧል፡፡
ይህንን ውጤት ተከትሎም ሰለሞንን ወክሎ እየተከራከረለት ያለው ብሪስቶም ሜየር የተባለው ጠበቃው ፖሊስ የሰራው ስራ እጅግ አሳፋሪ እንደሆነና ምንም እርግጠኛ መሆን በማይቻልባቸው የሜዳ ላይ ሙከራዎች ብቻ አንድን ሰው ሰክሯል ወይንም በአልኮልና አደንዛዥ ዕጽ ተጽዕኖ ውስጥ ነው ብሎ ማሰር ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህ ክስም ውድቅ እንዲሆንና ደንበኛቸውን ፍርድ ቤቱ በነጻ እንዲያሰናብትላቸው ጠይቀዋል፡፡ አልፎ ተርፎም የፖሊስ የመንገድ ላይ የስካር ምርመራዎች መፈተሽ አለባቸውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአውስቲን ቴክሳስ ፖሊስ በበኩሉ የሀኪም ውጤቱ እንደደረሳቸውና አረጋግጠው ከቬሂኩላር ሆሚሳይድ ዩኒት (የመኪና ነፍስ ማጥፋት መርማሪ ቡድን) እና ከትራቪስ ካውንቲ አቃቤ ህግጋ በመሆን የክሱን ይዘት ለመቀየር እየሰሩ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ አደጋው አሁንም በምርመራ ላይ እንደሆነም ታውቋል፡፡
የሟች ቤተሰቦች በመጀመሪያው የፖሊስ ሪፖርት መሰረት ሰለሞን ላይ የ 50 ሚልየን ዶላር ካሳ ክስ መስርተው ነበር፡፡
የሰለሞን ጠበቃ በዚህ ሳምንት ክሱ እንዲቋረጥ ፍርድ ቤቱን እንደሚጠይቁ አስታውቀዋል፡፡ ዛሬ ማክሰኞ ባስገቡት ማመልከቻም የሰለሞን የሀኪም ሪፖርት በግልጽ ሰለሞን ሰክሮ እንዳልነበር ስለሚያረጋግጥ ዳኛው ክሱን ሙሉ ለሙሉ እንዲያቋርጡ ወይንም ደሞ ለደንበኛቸው የዋስ መብት ከ1ነጥብ 2 ሚልየን ዶላር በአንድ ክስ አንድ ዶላር ብቻ እንዲጠየቅበትና በተከሰሰባቸው 7 ክሶች ልክ በ7 ዶላር ዋስትና እንዲፈታና ጉዳዩ ከውጭ ሆኖ እንዲከታተል ጠይቀዋል፡፡
ሲቢኤስ ኦስቲን በጉዳዩ ላይ ያናገራቸውን ባለሞያ ቃለ መጠይቅ ላይ ክሱ ለፖሊስ አሁን ከባድ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡