
በመጪው አርብ ፌብሯሪ 14 የሚከበረውን የፍቅረኛሞች ቀን (ቫለንታይን ዴይ) የሚያከብሩ ሰዎች ራሳቸውን ከአባላዘር በሽታ እንዲጠብቁና እንደ ኮንዶም ያሉ መከላከያዎችን ሳይጠቀሙ የግብረስጋ ግንኙነት እንዳይፈጽሙ የአሌክሳንድርያ ከተማ ጤና ቢሮ አሳስቧል፡፡
በተለይም በከተማው እየተበራከተ የመጣውን የኣባላዘር በሽታ ከግምት በማስገባት ሰዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንዲሁም አስፈላጊውን የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ መክሯል፡፡ ከ2010 ወዲህ በአሌክሳንድርያ ከተማ እንደ ጨብጥ፤ ቂጥኝና የመሳሰሉት የአባላዘር በሽታዎች እየጨመሩ እንደሆነ የቨርጂንያ ጤና ዲፓርትመንት ዳታ ያሳያል፡፡ የዚህ ምክንያት በትክክል ምን እንደሆነ ባይታወቅም መከላከያ መንገዶቹ ኝ እንደሚታወቁና ነዋሪዎች እኚህን መከላከያ መንገዶች እንዲጠቀም የአሌክሳንድርያ ከተማ ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡

ከነዚህም አንዱና ዋነኛው የመከላከያ መንገድ በግብረስጋ ወቅት ኮንዶም መጠቀም እንደሆነም የአሌክሳንድርያ ጤና ዲፓርትመንት ነርስ ማናጀር የሆኑት ፌሊሽያ ቤንዶልፍ ሲመንስ አስታውሰዋል፡፡ የኮንዶም ተወዳጅነት የቀነሰበት ዋነኛ ምክንያት ተብሎ የሚገመተው እርግዝናን የሚከላከሉ የተለያዩ አይነት ዘመን አመጣሽ አማራጮች ቁጥር መጨመር ነው። ባለሞያዋ አክለውም “መረሳት የሌለበት የወሊድ መቆጣጠሪያ እርግዝናን ብቻ እንደሚከላከልና የአባላዘር በሽታን እንደማይከላከል መታወቅ አለበት” ያሉ ሲሆን አክለውም PrEP የተባለው መድኃኒት ደሞ ኤች አይ ቪን ብቻ እንደሚከላከል አስገንዝበው ሌሎች የአባላዘር በሽታዎችን ለመከላከል ሰዎች ኮንዶምን መጠቀም እንደ አማራጭ ሊወስዱት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ነጻ ኮንዶሞች በ ዴል ፔፐር ኮሚውኒቲ ሪሶርስ ሴንተር መጸዳጃ ቤቶች ውስጥ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
መረጃውን ያገኘነው ከአሌክሳንድርያ ከተማ መንግስት ነው፡፡