
የዋሽንግተን ዲሲ መንግስት ቺፍ ፋይናንሺያል ኦፊሰር ግሌን ሊ ትላንት እንዳስታወቁት ከሆነ አመቱ ከተጀመረ እስካሁን ከተተነበየው በ21.6 ሚልየን ያነሰ ገቢ እንደተገኘና የፌደራል ሰራተኞች ከስራ መቀነስንና የቤት ግዢ ዋጋ መቀነስን አስመልክቶ ቀደም ሲል ከነበራቸው የገቢ ትንበያ በ342.1 ሚልየን ያነሰ ገቢ እንደሚኖራቸውና ይህም ለቀጣይ ተከታታይ 3 ዓመታትም በኔጋቲቭ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። ይህም በከተማዋ ሪሴሽን መለስተኛ ሪሴሽን እንደሚያስከትል ጠቁመዋል።

ይህን መረጃ ተከትሎም የዲሲ ካውንስል ሊቀመንበር የሆኑት ፊል ሜንደልሰን መጪው የበጀት ሂደትን ከባድ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል። አክለውም “ለዲሲ ብቻ የሚሆን የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል እንደሚያስከትል (recession)ና በተለይም ከሚስተዋለው የዋጋ መናርጋ ተያይዞ የዲሲ ከንቲባና ካውንስል ከመጪው ዓመት በጀት ላይ ቅነሳ ሊኖር እንደሚችልና አንዳንድ አገልግሎቶች ከናካቴው ሊቋረጡ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

የዲሲ ከንቲባ ሚውሪየል ባውዘር በበኩላቸው የፌደራል ሰራተኞች ቅነሳ ተጽዕኖው በዲሲና አካባቢው እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያየ መንገድ እንደሚገለጥና የዲሲ የገቢ ትንበያውም ይህን እንደሚያሳይ ተናግረዋል። አክለውም የቀጣይ ዓመት በጀታችንንም ይህንን ባገናዘበ መልኩ እንደሚዘጋጅና ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ ከዲሲ ካውንስል አባላትና ሌሎች ባልደረቦችጋ እንደሚወጡት በቀጣይም የዲሲን ኢኮኖሚ የሚያጎለብቱ ኢንቨስትመንቶችን ወደ ዲሲ እንዲመጡ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የዲሲና አካባቢው ኢኮኖሚ እስከ 40% የሚገመተው በፌደራል መንግስት ቅጥር ላይ የተመሰረተ ነው ተብሎ ይታመናል። ይህም በ1970ቹ እንደነበሩት የብረት ፋብሪካዎች አብዛኛው ተቀጣሪ በዚህ አንድ ተቋም ላይ የተንተራሰ እንደመሆኑ ይህ ሲናጋ አካባቢው ላይ ያሉ እንደ መደብሮች፤ ምግብ ቤቶች፤ የታክሲና ተመሳሳይ አገልግሎት ሰጪዎች የገቢ መቀነስ ሰለባ ይሆናሉ።
አልፎ ተርፎም ተቀናሽ ሰራተኞች ወደ ኡበርና ሊፍት የመሳሰሉ ስራዎች ሊሰማሩ እንደሚችሉና ከኡበርና ሊፍት የሚገኘው ክፍያ ብዙ ሰራተኛ በመኖሩ ምክንያት ሊያሽቆለቁል እንደሚችል እንደሚገመትም ተተንብዩአል። አንዳንዶች ደሞ ወደ ምግብና የመሳሰሉት የዴሊቨሪ ስራዎች እንደሚሰማሩ የሚገመት ሲሆን ሆኖም ሬስቶራንቶች ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ያህል ገበያ ስለማይኖራቸው ስራው እንደወትሮ አትራፊ ላይሆን እንደሚችል አልፎ ተርፎም ብዙ ሰዎች ስራውን ስለሚቀላቀሉ ይህም ዘርፍ ቶሎ ሊሞላ እንደሚችል እንደሚገመት ባለሙያዎች ተንብየዋል።