
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሁለተኛው የሥልጣን ዘመን ከጀመረ አንስቶ፤ ባለፉት አምስት ሳምንታት ከ30 ሺህ በላይ የፌደራል ሰራተኞች ስራቸውን ማጣታቸው ይገመታል። የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር አላስፈላጊ የመንግስት ወጭዎችን እና በጀቶችን እንዲሁም መረሃግብሮችን በመቀነስ ወደ ተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ማደግ እንደሚቻል በተደጋጋሚ በማሳወቅ የሰራተኛ ቅነሳው የሚቀጥል መሆኑን አስታውቋል።
የፌደራል መንግስት መቀመጫ በሆነችው ዲሲ እና በአካባቢዋ የሚገኙት ግዛቶችም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፌደራል መንግስት ተቀጣሪዎች የሚገኙባቸው አካባቢዎች ሲሆኑ፤ ከአንድ ቤት ሁለቱም የቤተሰብ አባላት የፌደራል ሰራተኞች የሆኑባቸው አሉ።
ይኸን ተከትሎ ዋሺንግተን ዲሲ ፣ ሜሪላንድ እና ቨርጂኒ ዜጎች እና ቤተሰቦች ከተጋረጠባቸው ድንገተኛ ችግር ለመታደግ አማራጭችን በማዘጋጀት ላይ ይገኛሉ።
ዋሺንግተን ዲሲ
በመዲናዋ ዋሺንግተን ዲስ ነዋሪ ሆነው ስራቸውን ካለጥፋታቸው ያጡ እና የለቀቁ የፌደራል መንግስት ሰራተኞች የሥራ ፍለጋ እና የቅጥር አማራጮችን job training and career counseling ድረገጽ ላይ ማግኘት እንደሚችሉ የዲሲ አስተዳደር አስታዉቋል።
የዲሲ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ዜጎች ሥራ እስኪያገኙ ድረስ ለ26 ሳምንታት በየሳምንቱ የሥራ አጥነት ክፍያ ድጎማ $444Tእንደሚያገኙ ተገልጿል። የከተማዋ ነዋሪ የሆኑ ዜጎች የስራ አጥነት ክፍያን እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን በተመለከተም https://unemployment.dc.gov/ ድረ ገጽ ላይ እንዲከታተሉ ተመክሯል።
ሜሪላንድ
በተመሳሳይ ከቀናት በፊት በፌብሩዋሪ 28/ 2025 ቀን የሜሪላንድ ሀገረ ገዥ ዌስ ሙር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ‘ከፌደራል መንግስት ጋር አብሮ ለመስራት እንጂ ለማጎብደድ ፍላጎት የለኝም’ በማለት ተናግረዋል። ሀገረ ገዥው በግዛታቸው ለሚገኙ እና ከፌድራል ስራቸው ለሚፈናቀሉ ዜጎች ጊዜያዊ መፍትሄ የሚሰጡ መርሃግብሮች እና የስራ ዕድል መፈለጊያ ድረ ገጾች መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።
ሥራቸውን የለቀቁ የሜሪላንድ ነዋሪዎች https://response.maryland.gov/federalpublicservants/ ድረ ገጽን በመጠቀም የተለያዩ ድጋፎችን እና ተጨማሪ መረጃዎችን ማግኘት ይችላሉ።
በራሳቸው ጥፋት ባልሆነ ምክንያት ስራ አጥ የሆኑ የፌደራል ሲቪል ሰራተኞች ለፌደራል ሰራተኞች የስራ አጥነት ካሳ (UCFE) ማመልከት ይችላሉ። ሌሎች ብቁ ሰራተኞች በመደበኛ ወይም የሥራ አጥነት መድህን (UI የአንኢምፕሎይመንት ኢንሹራንስ) መርሃግብር በኩል ማመልከት ይችላሉ።
ሜሪላንድ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ለሚፈልጉ ወይም እንደገና ለመቀጠር ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰራተኞች በድረገጽ እና በአካል የድጋፍ አገልግሎት እንደሚሰጥ በድረገጹ ላይ ሰፍሯል። አገልግሎቶቹ የስራ ማመልከቻ ወርክሾፖች፣ በግል የሚደረግ የስራ ማማከር፣ የሙከራ ቃለ-መጠይቆች፣ የሙያ እና የክህሎት ምዘና፣ የስራ ፍለጋ ስልት ስልጠናዎች፣ የሥራ ማጣት እና ከአንድ ሥራ ወደ ሌላ በሚደረግ የሽግግር ወቅትን የመቋቋም ድጋፍ፣ የድረገጽ ድጋፍ፣ እና ሌሎችንም ያካትታሉ።
በግዛቱ ያሉ ስራዎችንም https://www.jobapscloud.com/MD/ በዚህ ድረገጽ ላይ ማየት ይቻላል።
ቨርጂኒያ
በተመሳሳይ የቨርጂኒያ ግዛት ሀገረ ገዥ ግሌን ያንግኪን VirginiaHasJobs.com የተሰኘ ድረገጽ በማዘጋጀት ከ250 ሺህ በላይ የስራ ማስታወቂያዎችን ማዘጋጀታቸውን ከሰሞኑ ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል። ድረገጹም የቨርጂኒያ ነዋሪ ሆነው የፌደራል ሥራቸውን ለለቀቁ ሰዎች ቨርጂኒያ ግዛት ውስጥ በመሆን የስራ ቅጥር ማስታወቂያዎች ወዳወጡባቸው ኢንዲድ (indeed) እና ሊንክዲን የመሳሰሉ ማኅበራዊ ገጾች የሚያመራ መሆኑን ገልጿል።
በድረገጹ ላይ መመዝገብም የስራ ዕድሎችን መፈለግን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን VocationalRehabilitation ለማግኘት እንደሚረዳም አስታውቀዋል። https://www.virginiaworks.gov/job-seekers/
በተጨማሪም ድረ ገጹ ዜጎች ከስራ እስኪባረሩ ድረስ ሳይጠብቁ ከአሁኑ የስራ ልምዳቸውን እንዲያደራጁ እና ማመልከቻዎችን እንዲያዘጋጁ ይጠቁማል።
በቨርጂያ ግዛት ትልቁ ሳምንታዊ የሥራ አጥነት የገንዘብ ድጋፍ (አን ኢምፕሎይመንት) ክፍያ በሳምንት $387 በዓመት 20 ሺህ መሆኑም ተገልጿል።