
በቨርጂኒያ ግዛት ፍሬድሪክስበርግ የሊ ሂል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የሥስተኛ ክፍል ተማሪ መማሪያ ክፍል ውስጥ መሳሪያ ማምጣቱን ተክትሎ፤ ወላጆቹ በቁጥጥር ስር ውለው ክስ እንደተመሰረተባቸው የስፖትስልቫኒያ የፖሊስ ጽህፈት ቤት ገልጿል።
ታዳጊው የጠዋት ስናክ ለመብላት እጁን ቦርሳ ውስጥ ከቶ በሚፈልግበት ሰዓት መሳሪያው መባረቁን ፖሊስ አስታውቋል። የፖሊስ ሃላፊ ሜጀር ኤሊዛቤት ስካት “መሳሪያ ታጣቂዎች እንዲህ ዓይነት ክስተት እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው” በማለት አሳስበዋል።
ፖሊስ ሰኞ ዕለት ከጠዋቱ 11 ሰዓት በፊት በተፈጠረው ክስተት ማንም አለመጎዳቱን ገልጾ፤ ስፍራውን እየተጠበቀ ተማሪዎች ክፍሉን ለቀው መውጣታቸውን ገልጿል።
የታዳጊው ሁለቱም ወላጆቹ የአምስት ሺህ ዶላር ቦንድ እንዲከፍሉና የፊታችን አርብ በስፖትስላቬኒያ ካውንቲ የታዳጊዎች እና የቤት ውስጥ ጉዳይ ፍ/ቤት እንዲገኙ ታዘዋል።
የተማሪው መምህር ማንነታቸው ባይገለጽም በፍጥነት ተማሪዎቹን በማሰባሰብ እና ደህንነታቸውን በመጠበቅ ለወሰዱት እርምጃ ሙገሳ ተችሯቸዋል።
ፖሊስ አስፈላጊው የምክር እና የማረጋጋት አገልግሎት ለሊ ሂል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች መምህራን እና ወላጆች እየተሰጠ መሆኑም ገልጿል