
በሜሪላንድ ግዛት ውስጥ የሞንጎመሪ ካውንቲ ፖሊስ በኢሚግሬሽን አስገዳጅ አፈጻጸም ስራዎች ውስጥ በመግባት ህገወጥ ስደተኞችን ማሰስ እና ማሰር ውስጥ እንደማይሳተፍ የካውንቲው የሥስተኛ እዝ አዛዥ የሆኑት ጄሰን ኮኪኖስ በዚህ ሳምንት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ኮኪኖስ አቋማችን አይለወጥም ብለዋል።
በተመሳሳይ የሞንጎመሪ ካውንቲ ም/ቤት ፕሬዝዳንት ኬት ስቱዋርት የኮኪኖስ አቋም ደግፈው ያንጸባረቁ ሲሆን፤ በዚሁ ሳምንታዊ አጭር መግለጫ ላይ፣ ማንኛውም ሰው – ምንም ዓይነት የኢሚግሬሽን ሁኔታ ላይ ቢሆንም ሊያሳበው የሚገባው የህዝብ ደህንነት ስጋት ብቻ መሆኑን በመግለጽ ነዋሪዎች ሳይፈሩ የሚጋጥሟቸውን የህግ ጥሰቶች በአግባቡ እንዲያመለክቱ አሳስበዋል።
ኮኪኖስ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ በቅርቡ በሎንግ ብራንች፣ ብዙ ስደተኞች ባሉበት ሰፈር ውስጥ በተደረገ የማኅበረሰብ ስብሰባ ላይ ተሳትፈው እንደነበር በመግለጽ ሰዎች ያለፍርሃት ከፖሊሶች ጋር ስላለባቸው ስጋት ሲነጋገሩ ማየታቸው እና ያለው መቀራረብ እንዳሰደነቃቸው ገልጸዋል።
የሞንጎመሪ ካውንቲ ፖሊስ ዲፓርትመንት የዩናይትድ ስቴትስ የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ አስፈጻሚ አይስ የአካባቢ ህግ አስከባሪ መኮንኖችን እንዲጠቀም የሚፈቅደውን የኢሚግሬሽን ስምምነት 287(g) ውስጥ ተሳታፊ አይደለም።
የካውንቲው ፖሊስ ሦስተኛ እዝ ክፍል ሲልቨር ስፕሪንግ፣ ዋይት ኦክ እና በርተንስቪልን አካባቢዎችን የሚያጠቃልል ነው።
በተያያዘ የቨርጂንያ ገቨርነር የስቴት ፖሊሶች እንዲተባበሩ መፍቀዳቸውን ተከትሎ ተመሳሳይ ህጎች እንደ ላውደን ካውንቲ ባሉ የቨርጂንያ አካባቢዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡