
የዲሲ ፖሊስ ትላንት ሰኞ ፌብሯሪ 3 2025 ባወጣው መግለጫ በዲሲ ሳውዝ ኢስት የተከሰተን የግድያ ወንጀል እያጣራ እንደሆነ አስታውቋል።
ፖሊስ በመግለጫው እንዳሳወቀውም ዕሁድ ፌብሯሪ 2 2025 ለሊት 3፡03am ላይ የ7ኛ ዲስትሪክት ፖሊሶች በ2400 block of Martin Luther King Jr., Avenue, Southeast አካባቢ ተኩስ አለ ተብለው ይሄዳሉ። በቦታው ሲደርሱም አንድ አዋቂ ሰው በመኪናው ውስጥ እንዳለ በጥይት ተመቶ ያገኛሉ።
በቦታው የደረሱት የዲሲ እሳትና ድንገተኛ አደጋ ተከላካዮች የተጎጂውን ነፍስ ለማዳን የቻሉትን ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው በመቅረቱ ግለሰቡ ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል።
ፖሊስ በመግለጫው ሟች የአሌክሳንድርያ ነዋሪ የነበረው የ37 አመቱ አለም መድምም እንደሆነም አክሎ አስታውቋል።
በዚህ ወንጀል ላይ ተጨማሪ መረጃ ያለው ሰው በስልክ ቁጥር (202) 727-9099 በመደወል ወይንም በ50411 በቴክስት ጥቆማ መስጠት እንደሚችል አስታውቋል። የዲሲ ፖሊስ ይህን ወንጀል የፈጸመውን ሰው ማንነት ለጠቆመና ላሳሰረ ሰው እስከ 25,000$ ወሮታ እከፍላለሁ ብሏል።